በደብረ ማርቆስ ከተማ ትናንት በተካሄደ ብጥብጥ በሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል

ባህር ዳር ሀምሌ 5/2010 በደብረ ማርቆስ ከተማ ትናንት በተካሄደ ብጥብጥ በሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳትና በንብረት ላይ ውድመት መድረሱን የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዳስታወቁት በግርግርና ሁከቱ በሦስት ሆቴሎች ፣ በሁለት የፋይናንስ ተቋማት ፣ በአንድ ቤት እንዲሁም በ10 ተሽከርካሪዎች ላይ ውድመት ደርሷል። ከእዚህ በተጨማሪ ሁለት ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሕክምና ተቋም መላካቸውን ነው የገለጹት። በአሁኑ ወቅትም  በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ግርግር እንዲስፋፋ ከፍተኛ የቅስቀሳ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎች እየደረሱ መሆናቸውንም አቶ ንጉሱ አመልክተዋል። ችግር እየተከሰተ ያለው ምንም አይነት መረጃ በሌለበት ሁኔታ እንደሆነ ገልጸው ፤ ይህም እራስን በራስ ማጥፋት በመሆኑ ድርጊቱ በአፋጣኝ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋ። ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ባልተጨበጠ መረጃ ክልሉ የብጥብጥ ማዕከል እንዳይሆን በሚደረገው ጥረት ሁሉ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም አቶ ንጉሱ በግል ፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ጨምረው ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም