ቀጥታ፡

አዲሱ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ከጦርነት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ የማይፈታ ነገር አለመኖሩን ለዓለም ህዝብ አሳይቷል- አስተያት ሰጪዎች

ሐምሌ 5/2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል አዲስ የተከፈተው የግንኙነት ምዕራፍ አለመግባባቶችን ከጦርነት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ የመፍታቱን አዋጪነት ለዓለም ህዝብ ማሳየቱን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላትና የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች ተናገሩ፡፡ አሁን በመላ ሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥና መነቃቃት ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አስተያየት ሰጪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባሉ  ሀጂ ተሻለ ኬሮ እንዳሉት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚመራው ልዑክ አስመራ የተደረገለት ህዝባዊና መንግሥታዊ አቀባበል የተለየ የደስታ ስሜት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ከአሳዛኝ ጦርነትና ከ20 ዓመታት የጥላቻ ጉዞ ብኋላ የተደረገው አዲስ የሰላምና በጋራ የመልማት ስምምነት ከጦርነትና ከመሳሪያ እሽቅድምድም ይልቅ በሰላማዊ መንገድ የማይፈታ አለመግባባት  እንደማይኖር ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሀጂ ተሻለ የሁለቱን ሀገራት የሻከረ ግንኙነት ከማደስ በተጨማሪ ባለፉት ሶስት ወራት የመጣው ለውጥ አባላቱ “ከመፈራራት” ወጥተው ትክክለኛውን የህዝብ ችግር ነቅሰው እንዲያወጡ በር እንደከፈተላቸውም ተናግረዋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብና ፖለቲከኞች ከራሳቸው ጥቅም ይል              ቅ ለሀገርና ህዝብ የጋራ ተቃሚነት ተግተው የመስራት ጅምራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው ሀጂ ተሻለ የጠየቁት፡፡ ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሮዳስ ሱልጣንም ሰላም ከራስ ጀምሮ ወደ ቤተሰብና ሀገር እያደገ እንደሚሄድ ገልጸው፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል እየሰፈነ ያለው ሰላም ለሁለቱም ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ሮዳስ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቶች የበለጠ ኃላፊነትና ትኩረትም እንዲሰጣቸው የሰጡት አጽንኦት ምክር ቤቶቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡና የህዝቡ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችም በአግባቡ እንዲስተናገዱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡ ህዝቡ የሚፈልገውን ለውጥና ልማት ለማረጋገጥ አስቀድሞ የሀገሪቱ ሰላም አስተማማኝ መሰረት እንዲይዝ  ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው የምክር ቤቱ አባል የገለጹት፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው የሰላምና የትብበር ግንኙነት ለፍሬ እንዲበቃ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ እርሳቸውም በቀጠናው የሚስተዋለው የሰላም እጦት ለዜጎች ስደትና ድህነት ምክንያት በመሆኑ የሁለቱ ሀገራት አዲስ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቲያትሪካል አርት የመጀመሪያ ዲሪዋን ያገኘችው ዘወትር ግርማ አሁን በሀገሪቱ እየታየ ያለው የሰላምና የትብብር መንፈስ በሙያዋ የድርሻዋን ለማበርከት እንዳነሳሳት ገልጻለች፡፡ በፍቅርና ይቅርታ ላይ የተመሰረተው ብሔራዊ መግባባት የፈጠረው መነቃቃት ወደ ኋላ እንዳይመለስ የአካባቢዋን ሰላም በንቃት እንደምትጠብቅም አረጋግጣለች፡፡ በማይክሮ ባዮሎጂ የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂው አስናቀ ደሳለውም በተመሳሳይ “ከምንጊዜውም በላይ የደመቀውን ኢትዮጵያዊነት” ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም