መኖሪያ ፈቃዳቸውን የተቀሙ ኢትዮጵያዊያን ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ መኖሪያ ፈቃድ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻቸ - ኢዜአ አማርኛ
መኖሪያ ፈቃዳቸውን የተቀሙ ኢትዮጵያዊያን ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ መኖሪያ ፈቃድ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻቸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17/2012 (ኢዜአ) በሳዑዲ ዐረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን (ኢቃማ) የተቀሙ ኢትዮጵያዊያን ፈቃዳቸው ለምን እንደተቀማ እስኪጣራ ድረስ የኢቃማ ካርድ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን በአገሪቷ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
ባለፉት ጥቂት ሣምንታት በሳዑዲ ዐረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ "ማንፋሐ" እና "ነሲ" በተባሉ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት ባደረጉት ፍተሻ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) ያላቸውና የሌላቸውን ኢትዮጵያዊያን መያዛቸው ይታወሳል።
በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢቃማ እያላቸው የተቀሙ ዜጎች ካሉ ማስረጃቸውን ይዘው ከነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለኤምባሲው እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጎ ነበር።
በቀረበው ጥሪ መሠረትም እስካሁን ድረስ "ኢቃማችን ተቀምቷል" ያሉ 24 ኢትዮጵያዊያን ማስረጃ ይዘው መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቀደም ሲል መዘገቡ የሚታወስ ነው።
ኤምባሲውም የቀረበለትን ማስረጃ ይዞ ከሪያድ የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ለመምከር ቀጠሮ ይዞ እንደነበርም አይዘነጋም።
በዚሁ መሠረት የኤምባሲው የሥራ ኃላፊዎችና የሪያድ የፀጥታ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ መወያያታቸውን በሥፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በውይይቱም የሪያድ የፀጥታ ኃላፊዎች አፈሳውና አሰሳው ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ በሌላቸው ላይ ያነጣጠረ ነበር ማለታቸውን ተገልጿል።
ይሁንና ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) እያላቸው ኢቃማቸው የተወሰደ ዜጎች የመኖሪያ ፈቃዳቸው ለምን እንደተቀማ እስኪጣራ ድረስ አሰሪዎቻችውን ይዘው በሳዑዲ ዐረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የፓስፖርት ጠቅላይ ዳይሬክቶሬት (ጃዋዛት) ቀርበው ያለ ምንም ክፍያ የኢቃማ ካርድ መውሰድ እንደሚችሉ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል።
ማንኛውም ሕጋዊ ነዋሪ የሳዑዲ ዐረቢያን ሕግ አክብሮ እስከኖረና ሕገወጥ ድርጊቶች እስካልፈጸመ ድረስ መያዝ እንደሌለበትም በውይይቱ ወቅት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱም ተመልክቷል።
በተደጋጋሚ ጊዜ አፈሳ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኤምባሲው በመግለጫው አሳስቧል።
በሳዑዲ ዐረቢያ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎችን የኢትዮጵያ መንግሥት ወደአገራችው ለመመለስ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ካደረገ በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ በሳዑዲ ዐረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ በቅርቡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በሳዑዲ ፀረቢያ ሕግ መሠረት ያለምንም ምክንያት ኢቃማ ወይም ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያለውን ሰው ማሰርና የመኖሪያ ፈቃዱን መቀማት የተከለከለ ነው።
ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወይም በቱሪስት ቪዛ (ዚያራ) ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የገቡና ከሥራ ገበታ ጠፋ በሚል ክስ የተመሠረተባቸው ኢትዮጵያውያን የመውጫ ቪዛ አያገኙም ነበር።
በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ዐረቢያ የመንግሥት አካላት ጋር ተነጋገሮ በተጠቀሱት ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ያልቻሉ ዜጎች የመውጫ ቪዛ እንዲያገኙ ሥምምነት ላይ መድረሱን መግለጫው አስታውቋል።
ኢትዮጵያዊያኑ ከኤምባሲው የድጋፍ ደብዳቤ በማጻፍ የጉዞ ሂደቱን መጀመር እንደሚችሉ ያመለከተው መግለጫው፣ ኤምባሲው የመውጫ ቪዛ ማግኘት የሚቻልባቸውን መሥፈርቶች ማስቀመጡንም አመልክቷል።
ዜጎች ፓስፖርት ወይም የአንድ ጊዜ የጉዞ ሰነድ (ሊሴ ፓሴ) መያዝ እንዲሁም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ነፃ መሆንን የሚያሳይ የፒ.ሲ.አር ምርመራ ውጤት ማስረጃ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁሟል።
የፒ.ሲ.አር ምርመራ ውጤት ማስረጃ የያዘ ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ መንግሥት ወዳዘጋጀው ለይቶ ማቆያ መግባት ሳይጠበቅበት የግል መኖሪያ ቤቱን እንደ ለይቶ ማቆያ መጠቀም እንደሚችል ተገልጿል።
ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የአንድ ጊዜ ጉዞ ትኬት መግዛት እንዳለባቸውም ኤምባሲው አስታውቋል።
ኢትዮጵያዊያኑ መቼ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ በመግለጫው ላይ የተባለ ነገር የለም።