ቀጥታ፡

ኤምባሲው በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ የሚያደርጉበትን የባንክ ሐሳብ ከፈተ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17/2012(ኢዜአ) "ኢትዮጵያችን በብርሃን ትደምቃለች" በሚል መሪ ሀሳብ በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቷ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ የሚያደርጉበትን የባንክ ሒሳብ መክፈቱን አስታወቀ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ እንዲያደርጉ የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸገጋሩን አምባሳደር ፍጹም ገልጸዋል።

"የግድቡ መጠናቀቅ በጨለማ ያለ ህዝብ ብርሃን እንዲያይ ለማድረግና የኤሌትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን በመጨመር ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ያለው ሚና ወሳኝ ነው" ብለዋል።

ግድቡ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድሎች በመፍጠርና በእንጨት ለቀማና በጭስ ለሚንከራተቱና ለሚሰቃዩ እናቶች ትልቅ እፎይታን እንደሚፈጥርም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ያስገኛል።

የሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም መገንባቱ ለኢትዮጵያዊያን እጅጉን የሚያኮራ እንደሆነና ለግድቡ ግንባታ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊያን ድጋፉቸውን በማሳየት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ለግድቡ በሚፈለገው መልኩ ድጋፍ ማድረግ ያልቻሉ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት ዕድል እንዲመቻችላቸው ሲጠይቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚሁ መሰረት ኤምባሲው "ኢትዮጵያችን በብርሃን ትደምቃለች" በሚል መርህ በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ የሚያደርጉበትን የባንክ ሒሳብ መክፈቱን አምባሳደር ፍጹም ገልጸዋል።

Citi bank N.A አካውንት ቁጥር 15655873 እና በኤምባሲው ድረ ገጽ ላይ በሚገኘው የ" PayPal " አማራጭ አማካኝነት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆች በተቀመጡት አማራጮች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ አምባሳደር ፍጹም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በሌላ በኩል በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት በአሌክሳንድርያ ከተማ በምትገኘው የኢትዮጵያዊያን ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በፀሎት መርሃግብር ላይ የታደሙ ምዕመናን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ "ከነሐሴ 8 እስከ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በቤተክርስቲያኗ የጸሎት መርሃግብር ላይ የተገኙ ምዕመናን በቫይረሱ እንደተያዙ በመስማታችን ሀዘን ተሰምቶናል" ብለዋል።

በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተጠቀሱት ቀናት የፀሎት መርግብር ላይ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ምዕመናን ለቫይረሱ ስለመጋለጣቸው ጥቆማ እንደደረሰውም ነው የገለጹት።


አምባሳደር ፍጹም እንዳሉት ለቫይረሱ ከተጋለጡት መካከል እስካሁን 7 ሰዎች በሆስፒታል የህክምና እርዳታ እያገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል ሦስቱ በጠና ታመው በጽኑ ህክምና ክፍል እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

በተጠቀሱት ቀናት በቤተክርስቲያኒቷ ከነበሩ ሰዎች መካከል በተደረገ ምርምራ እስካሁን ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ነው ያመለከቱት።

ሆኖም የአካባቢው የጤና ቢሮ ክትትል አድርጎ እስከሚያስታውቅ ድረስ ትክክለኛውን ቁጥር ማወቅ እንደማይቻል የተናገሩት አምባሳደር ፍጹም፣ ለታመሙ ሰዎች ፈጥነው እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በተጠቀሱት ቀናት በቤተክርስቲያኑ የነበሩ ሰዎች ወደ አሌክሳንደሪያ የጤና ቢሮ በመደወል ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

"በየትም ቦታ ብንሆን የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችና መንግስት የሚሰጡትን ምክር ባለመሰልቸት በመቀበል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል" ብለዋል።

ማህበረሰቡ የተጠናከረ ትስስር ስላለው ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረገ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቀላሉ ተጋላጭ ሊሆን እንደሚችልም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም