ቀጥታ፡

ለዶክተር ፍስሃዬ አለምሰገድ የመታሰቢያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17/2012(ኢዜአ) የአክሱም ዩኒቨርስቲ መምህር ለነበሩት ለዶክተር ፍስሃዬ አለምሰገድ የመታሰቢያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሄደ።

ዶክተር ፍስሃዬ ከአባታቸው አለምሰገድ ተስፋሚካኤልና ከእናታቸው ወይዘሮ ዝናብ ገብረእግዚአብሔር በአድዋ ወረዳ ግንቦት 5 ቀን 1970 ዓ.ም ነው የተወለዱት።

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በቀድሞ የኤርትራ ክፍለ ሃገር በሚገኘው አዲዃላ ከተማ የመዋዕለ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም አጠናቀዋል።

በመቀጠልም 1983 ዓ.ም የነበረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ወደ ባህርዳር በማቅናት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በብቃት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ወደ ጂማ ዩኒቨርሲቲ (ጤና ሳይንሰ ኮሌጅ) በመግባት በ1994 ዓ.ም ጠቅላላ ሓኪም ሆነው ተመርቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው መምህር ሆነው ከተቀጠሩበት 1995 ዓ.ም ጀምሮ ለ17 ዓመታት በማስተማር፣ በማማከርና የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት እስከ ተባባሪ ፕሮፈሰርነት ማዕረግ ደርሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከ50 የሚበልጡ ችግር ፈቺ ጥናቶችን ታዋቂ በሆኑ የአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጆርናሎች አሳትመዋል።

ጎን ለጎንም በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህርዳር፣ በአክሱም፣ በሃረር፣ በጎንደር፣ በቢሾፍቱ፣ በድሬዳዋ፣ በመቀሌና በሌሎችም ከተሞች ባሉ ተቋማት ሥልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ከለቀቁ በኋላም የአዲስ አበባ ከተማ የጤና ቢሮ አማካሪና ከዛም ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአክሱም ዩኒቨርስቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት እያገለገሉ ቆይተዋል።

ህይወታቸው እስካለፈችበት ጊዜ ድረስም በትግራይ ክልላዊ መንግሥት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) መረጃ ትንተናና ትንበያ ክፍል ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያሳያል።

የዶክተር ፍስሃዬ የልጅነት ጓደኛና የረጅም ዓመት የሥራ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አማረ ደርበው "ዶክተር ፍስሃዬ ለሙያው የተሰጠና የሥራ ፍቅር ነበረው'' ብለዋል።

በሥራ ላይ በቆዩባቸው ዓመታት በርካታ ሰዎችን ማፍራት መቻላቸውን ገልጸው፤ በተለይም በቡድን ሥራ የነበራቸው እምነት የሚያስመሰግናቸው እንደነበር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ህክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው በበኩላቸው ''ዶክተር ፍስሃዬ አንድ የጤና ባለሙያ ለአገሩ የሚያደርገውን ውለታ ውለዋል'' ብለዋል።

ምንም እንኳን የዶክተር ፍስሃዬ ህልፈተ ህይወት አሳዛኝ ቢሆንም ለአገራቸው ያበረከቷቸውና ያሳዩት ቁርጠኝነት ለብዙ የጤና ባለሙያዎች ኩራት መሆኑን አስረድተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ''ዶክተር ፍስሃዬ በሙያቸው ለአገራቸውም ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው'' ብለዋል።

በሙያቸው ያበረከቷቸው ሥራዎች በመጽሃፍ መልክ ተሰንደው ለቀጣይ ትውልድ ትምህርት እንዲሆን መቀመጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የዶክትር ፍስሃዬን የቀድሞ ህይወትና የሥራ ጊዜያት የሚያስታውሱ ዝግጅቶች የተካሄዱ ሲሆን የጸሎት መርሃ ግብርም ተካሂዷል።  

በመርሃ ግብሩ ላይም የሟች የቀድሞ የሥራ ባልደረቦች፣ አብሮ አደጎች፣ ዘመዶችና ቤተሰቦች እንዲሁም ወዳጆች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም