ቀጥታ፡

ለአገር በቀልና እየተመናመኑ ላሉ ዕፅዋቶች ትኩረት መስጠቱ ሥነ ምኅዳርን ለመጠበቅ የላቀ ጠቀሜታ አለው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17/2012 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለአገር በቀልና እየተመናመኑ ላሉ ዕፅዋቶች ትኩረት መስጠቱ ሥነ ምኅዳርን በአግባቡ ለመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

ከ135 በላይ አገር በቀል ዕጽዋቶች በመጥፋት ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት የደንና የግጦሽ መሬት ብዝሃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ዴቢሳ ለሜሳ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ሥራ ላይ ቅድሚያ ይሰጥ የነበረው ከውጭ ለመጡ ዕፅዋት ነበር።

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከተጀመረ ወዲህ ለአገር በቀል ዕፅዋት ትኩረት በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ኢኒስቲትዩቱ አንድ ሚሊዮን የተለያዩ አገር በቀል ችግኞችን በማዘጋጀት ከ775 ሺህ በላይ እንዲተከሉ ማድረጉንም ገልጸዋል።

አገር በቀል ዕፅዋትን መትከል የአካባቢ ሥርዓተ ምኅዳርና ሥነ ምኅዳርን በመጠበቅ በኩል ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ለአገር በቀል ዕፅዋት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በአገሪቱ ከተተከሉት ችግኞች አብዛኛዎቹ አገር በቀል እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።

የአገር በቀል ዕፅዋትን በስፋት ከመትከል በተጓዳኝ እየተመናመኑና በመጥፋት ላይ ላሉ ዕፅዋቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው ዶክተር ዴቢሳ አስረድተዋል።

ለዚህም በአገሪቱ በመመናመንና በመጥፋት ላይ የሚገኙ ከ135 በላይ የተለያዩ ዝርያ ዕፅዋቶች ከ10 ምኅዳሮች ተወስደው የመመለስ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢኒስቲትዩቱ በተለይ በመመናመን ላይ የሚገኙትን እንደ ዝግባ፣ ዋርካ፣ ጥቁር እንጨትና መሰል የደን ተክሎችን ጨምሮ ለባህላዊ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ዕፅዋቶችን በመንከባከብ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢኒስቲትዩቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራ የጠቆሙት ዶክተር ዴቢሳ፣ ከኢትዮጵያ የባህል መድኃኒቶች ማኅበር ጋርም በጋራ እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት የደንና የግጦሽ መሬት ብዝሃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት የደን ጅን ባንክ አስተባባሪ አቶ አባይነህ ለገሠ በበኩላቸው ዕፅዋቶችን ከጥፋት ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በአሁኑ ወቅት ከ350 በላይ አገር በቀል የተለያዩ ዕፅዋቶችን ከልዩ ልዩ አካባቢዎች አምጥቶ በጅን ባንኩ በማስገባት ከጥፋት ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ጅን ባንኩ አገር በቀል የሆኑ ዕፅዋትን ብቻ እንደሚይዝና በተለይ የኢኮኖሚ አዋጭነት ላላቸውን ዘሮች ይበልጥ ትኩረት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም