ቀጥታ፡

ማህበረሰቡ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳንሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግልን ይገባል---አካል ጉዳተኞች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17/2012(ኢዜአ) ማህበረሰቡ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳንሆን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች ገለጹ።

በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ በኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ ቫይረሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት ተዛምቶ ሚሊዮኖችን አጥቅቷል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችንም ሕይወት ቀጥፏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው በሎ ከለያቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል አካል ጉዳተኞች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

በዓለማችን ላይ ከ1 ቢሊዮን በላይ ወይንም 15 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ አካል ጉዳተኛ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ110 እስከ 190 ሚሊዮን የሚሆኑ ጎልማሶች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያለባቸው እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያም ከ18 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሄው የድርጅቱ መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት አካል ጉዳተኞችን ወደኋላ ገሸሽ ማድረግ የለበትም።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካለው ባህሪይ አንጻር ሰዎች ድጋፍ ሲያደርጉላቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ መሆን እንዳለበት ነው የገለጹት።

በማንኛውም ጊዜ ሰዎች ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ሲያደርጉ አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቅና የንጽህና መጠበቂያዎችን በመጠቀም ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳንይሆኑ ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በትራንስፖርት አገልግሎት ቅድሚያ ለአካል ጉዳተኞች መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች ለራሳቸው እንደሚጠነቀቁት ሁሉ ሌሎች ሰዎችም ለእነሱ እንዲጠነቀቁላቸው ነው የጠየቁት።

አቶ ዮሴፍ አዳነ፣ ወይዘሮ እቴነሽ ወርቂቾ እና ወይዘሮ በላይነሽ ዘለቀ

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ ፌዴሬሽኑ አካል ጉዳተኞች ለኮሮናቫይረስ ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ አስመልክቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልጸዋል።

ለእዚህም ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን ድጋፍ ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደችግሩ ስፋት እየታየ ተጨማሪ ስልጠና የሚሰጥ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከተለያዩ አካላት ድጋፍ በማሰባሰብ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አቶ አባይነህ ተናግረዋል።

መንግስትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አካል ጉዳተኞች ለቫይረሱ ተጠቂ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄና ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም አስገንዝበዋል።

በብሪታኒያ የብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤን.ኤች.ኤስ) የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ሰለሞን አማረ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማንንም ሳይለይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝና በይበልጥ አካል ጉዳተኞች በቫይረሱ የሚደርስባቸው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

"አካል ጉዳተኞችን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ዋንኛው መፍትሄ በቤታቸው እንዲቆዩ ማድረግና የሚፈልጉትንም አገልግሎት በቤት ውስጥ እንዲያገኙ ማድረግ ነው" ብለዋል።

አቶ ሰለሞን እንዳሉት አካል ጉዳተኞች አስገዳጅ ሆኖ ከቤታቸው የሚወጡበት ጉዳይ ካለ የሚረዷቸው ሰዎች አካላዊ ርቀትን መጠቀበቅና የእጅ ማጽጃ ኬሚካል በመጠቀም ጥንቃቄ ሊያደርጉላቸው ይገባል።

አካል ጉዳተኞች ራሳቸው ሳይዘናጉ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎችም በቤታቸውና በማቆያ ቦታ እንክብካቤ የሚያደርጉሏቸው ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት ባለሙያው፣ በተንቀሳቃሽ ምስልና ቀለም የተደገፉ መልዕክቶች ሊዘጋጁላቸው እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በብሪታኒያ የኮቪድ-19 ምልክቶች የታዩበት አካል ጉዳተኛ ወደ ጤና ተቋማት ሲደውል ፈጣን አገልግሎት እንደሚያገኝና ለአካል ጉዳተኞች ተለይቶ የተዘጋጀ የህክምና ቦታ መኖሩን ጠቁመው፣ ይህ ተሞክሮ በኢትዮጵያ ቢኖር መልካም መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

በቫይረሱ የተያዙ አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙበት አልጋና ለመፀዳጃ የሚያስፈልጉ ቦታዎች ለነሱ በሚስማማ መልኩ ሊዘጋጅ እንደሚገባም ነው ባለሙያው የተናገሩት።

በትራንስፖርት አገልግሎትም አካል ጉዳተኞች ለብቻቸው የሚቀመጡበት ቦታ መለየትና ለእነሱ ተብሎ የተዘጋጀ መግቢያ በር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

"የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶች በሚዘጋጁበት ወቅትም አካል ጉዳተኞች ሊረዱት በሚገባ መልኩ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

መንግስት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች በሚሰጡ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያረጉላቸው አቶ ሰለሞን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም