ባንኩ በኮቪድ-19 ምክንያት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብድር ሰጥቶት የነበረውን ወርሃዊ የክፍያ እፎይታ ጊዜ ማጠናቀቁን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በኮቪድ-19 ምክንያት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብድር ሰጥቶት የነበረውን ወርሃዊ የክፍያ እፎይታ ጊዜ ማጠናቀቁን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 17/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርኝሽ ምክንያት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብድር ተበዳሪዎች ሰጥቶት የነበረውን ወርሃዊ የክፍያ እፎይታ ጊዜ ማጠናቀቁን አስታወቀ።
የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ጫና ታሳቢ በማድረግ ባንኩ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብድር ተበዳሪዎች ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም የቆየ የሶስት ወር የእፎይታ ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል።
በመሆኑም የእፎይታ ጊዜው በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም መጠናቀቁንና ደንበኞች ክፍያቸውን ከሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ መክፈል መጀመር እንዳለባቸው ባንኩ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሶስት ወር የብድር እፎይታ ጊዜ መሰጠቱን አስመልክቶ አውጥቶት በነበረው መግለጫ የእፎይታ ጊዜ ቢሰጥም የብድር መክፈያ ጣሪያው እንደማይራዘም ገልጾ ነበር።
”ወርሃዊ ክፍያውን መክፈል አቅም ያላቸው ደንበኞች የወርሃዊ ብድር ክፍያቸውን እንዲከፍሉ ይበረታታሉ” ሲል ባንኩ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ባንኩ በሰጠው የእፎይታ ጊዜ ውስጥ 542 ሚሊዮን ብር ገንዘብ መሰብሰብ ይችል እንደነበር በመግለጽ፤ ”በወረርሽኙ ምክንያትም ወደቀጣይ ጊዜ አራዝሚያለሁ” ማለቱ የሚታወስ ነው።