ለታላቁ ሕደሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - የምዕራብ ጎንደር ዞን ባለሀብቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ ሕደሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - የምዕራብ ጎንደር ዞን ባለሀብቶች
መተማ፣ ነሐሴ 117/2012 (ኢዜአ) - በምዕራብ ጎንደር ዞን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከዚህ በፊት ካደረጉት አስተዋጽኦ የላቀ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዳቸውን በዞኑ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ለኢዜአ ገለጹ።
በዞኑ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በድል መጠናቀቁ በፈጠረው መነሳሳት ግማሽ ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ መፈጸሙ ተገልጿል።
በገንዳ ውኃ ከተማ በጥጥ መዳመጥ የተሰማሩት አቶ አብድልቃድር አህመድ እንደተናገሩት የሕዳሴው ግድብ ከነበረው የቁልቁለት ጉዞ ግንባታ ሂደት ተላቆ አሁን ባለበት ደረጃ መድረሱ የሚደነቅ ነው።
ግድቡ ለመላው ኢትዮጵያውያን የብርሃን ተስፋ በመሆኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ ከዚህ በፊት የ50 ሺህ ብር ቦንድ ያለወለድ መግዛታቸውን በማስታወስ አሁንም ወለድ የማይታሰብበት የ100 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
''አሁን ባለው ከፍተኛ የሆነ በኤሌክተሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር በሙሉ አቅማችንና ጊዜያችን መሥራት አልቻልንም'' ያሉት ባለሀብቱ ግድቡ ችግሩን ይፈታል በሚል እምነት መደገፋቸውን ገልጸዋል።
ግድቡ ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ቋሚ የኢትዮጵያ ቅርስ በመሆኑ ለግንባታው መጠናቀቅ የበኩሌን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል መፈጠር እንዳለበት ጠቁመዋል።
በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመነት የተሰማሩት አቶ ይላቅ መንግሥቱ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብን መጠናቀቅ በጉጉት እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
በግድቡ ግንባታ በተፈጠረ የአመራር ችግር በታቀደለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት መፈጠሩ እንዳሳዘናቸው አመልክተው፤ አሁን ከውስብስብ ችግር ተላቆ ውኃ በመያዙ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ለግንባታው የ30 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው፤ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎም የአምስት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የ50 ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ ግድቡ ተጠናቆ ሥራ እስኪጀምርም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
''ይህ ግድብ የሀገራችን ህልውና ነው፤ ለህልውናችን ደግሞ እንኳንስ ገንዘባችንን ደማችንንም እንሰጣለን'' ሲሉም አብራርተዋል።
ሌላኛው በገንዳ ውኃ ከተማ በሰሊጥ ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አምሳሉ ዓለሙ እንደተናገሩት የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እስከ አሁንም ከ60 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ግድቡ አሁን ከደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በተለይም አሁን የደረሰበት ደረጃ ለተጨማሪ ድጋፍ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመው፤ የ30 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የሚመለሱ ቦንዶችን በመጠቀምና ተጨማሪ ግዥ በመፈጸም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
“ባለሀብቶች የፕሮጀከቱን አስፈላጊነት በመረዳት ያለማንም ቀስቃሽነት ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው” ያሉት ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምቹ ወረቀት ናቸው።
በተለይም የመጀመሪያው ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ተከትሉ ባለፉት ወራት ግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ሽያጭ መፈጸሙን ተናግረዋል።
በቀጣይም እስከ ቀበሌ የማስተባበር ሥራ በመሥራት ኅብረተሰቡ ደጋፉን የሚያጠናክርበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተናግረዋል።