በአዋበል ወረዳ በተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በአዋበል ወረዳ በተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ
ደብረ ማርቆስ፣ ነሃሴ 16 /2012 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ ዛሬ ቀን ስምንት ተኩል አካባቢ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ መከላከልና ቁጥጥር የስራ ሂደት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አደጋው የደረሰው ከደጀን ከተማ ወደ አዋበል ወረዳ ሉማሜ ከተማ ይጓዝ የነበረ የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3--25041 አ.ማ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ወጀል ቀበሌ ሲደርስ በመገልበጡ ነው።
በአደጋው ሾፌሩና ረዳቱን ጨምሮ በተሽከርካሪው ውስጥ ከነበሩ ዘጠኝ ሰዎች መካከል የአራት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በቀሪዎቹ ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
ዋና ኢንስፔክተሩ እንደገለጹት ተጎጂዎች በሉማሜ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑንና የሟቾች አስከሬንም ለየቤተሰቦቻቸው መላኩን አስታውቀዋል።
በዞኑ በተሽከርካሪ አደጋ ሳቢያ የሰው ህይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም በተደጋጋሚ የሚከሰት በመሆኑ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ዋና ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል።