ቀጥታ፡

በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ

ሰመራ ነሐሴ 16/2012(ኢዜአ) "ሂታስ" በጎ አድርጎት ማህበር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች በገንዘብና ቁሳቁስ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት  አቶ ጋራድ መሀመድ ድገፉን ሲሰጡ  የአፋር ህዝብ ችግር የኛም ችግር ነው በሚል ወገናዊ  ስሜት ከተለያዩ አካላት ያሰባሰቡትን  ከ700ሺ ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ማህበሩ ካበረከታቸው መካከል ብርድልብስ ፣ ፍራ፣ ጀሪካኖችና የምግብ ማብሰያ እቃዎች ይገኙበታል

በቀጣይም ህብረተሰቡ ወደ መደበኛ ኑሮው እስኪመለስ  አስፈላጊውን ድጋፋ ለመስረገም  ቃል ገብተዋል።


የእግር ኳስ  ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ከተወያዩ በኋላ 300ሺብር በጥሬ ገንዘብ እና ቁሳቁስ  በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች እንዲውል በወሰኑት መሰረት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉ ትንሽ ቢሆንም ትልቁ መልዕክት ከገንዘቡ ባሻገር  አብሮነታቸንና አጋርነታችንን ለማሳየት ነው ብለዋል።

በአፋር ክልል በተከሰተው ጎርፍ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ሁሉም  ኢትዮጵያዊ በወንድማማችነት መንፈስ ያደረገው ድጋፍና ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ይሄው በጎ አድራጎት በሁሉም ዘንድ የበለጠ እንዲጎለብት አስተያየትቸውን ሰጥተዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ማህበሩና  ፌዴሬሽኑ በክልሉ ተገኝተው በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ላደረጉት ድጋፍ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም