ቀጥታ፡

ልዩነቶች በዘላቂነት መፈታት የሚችሉት በምክክር እንጂ በግጭት አይደለም ... የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 16/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የፖለቲካ ስብራቶች መፈታት የሚችሉት ሁሉን አቀፍ በሆነ ምክክር እንጂ በግጭት አይደለም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ፖለቲከኞች በመድረኮች የሚናገሯቸውን ሃሳቦች በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉም ነው ጥሪ ያቀረቡት። 

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሀገራዊ መግባባት ሂደት ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ አካሄደዋል።

መድረኩን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያዘጋጀው ሲሆን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት የተጀመረው የምክክር አካል መሆኑም ተገልጿል።

በመድረኩም 'የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ዳራ'፣ 'የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀማመር' እንዲሁም "ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊነት ለሀገር ግንባታ' የሚሉ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

ኢዜአ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲን ወክለው በመድረኩ የተገኙትን ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢን አነጋግሯል።

የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ቀጀላ መርዳሳ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ "የእኔ ሃሳብ ብቻ ካልሆነ" የሚል የግትርነት አካሄድ መኖሩን ተናግረዋል።

በፓርቲዎች መካከል የመከባበርና የውይይት ባህል አለመዳበሩን ገልጸው፤ አሁን ላይ ከተለመደው አካሄድ ወጥተን ችግሮቻችንን በሰለጠነ ውይይት መፍታት አለብን ነው ያሉት።

"ለዚህ ደግሞ ያሉንን ልዩነቶች አንጥሮ በማውጣት በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ መግባባት ሌሎቹ ላይ ደግሞ በልዩነት መውጣት ወይም ተስማምቶ መተው ይቻላል" ብለዋል።

ከዚህ አንጻር የተጀመረው የውይይት መድረክ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአብን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በበኩላቸው የፖለቲከኞች አንኳር ማዕከል 'ሀገርን ማትረፍ' መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።

በመሆኑም ፖለቲከኞች በውይይት መድረኮች ላይ የጋራ አማካኝ መፍጠር የሚያስችሉ ሃሳቦችን ይዘው መምጣት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

በዚህ ረገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፈለገው ልክ እየሄዱ አለመሆናቸውን ጠቁመው፤ የተጀመረው ሙከራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በመድረኮች ላይ የሚናገሯቸውና ዞር ብለው የሚፈጽሟቸው ተግባራት የሚለያይ ከሆነ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል የተናገሩት ደግሞ በመድረኩ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የቀረቡት ዶክተር አለሙ ስሜ ናቸው።

በፖለቲካ መድረክ ተፎካክረው ማሸነፍ የሚቻለው ሀገር ሲኖር ብቻ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርንና ህዝብን ማዕከል አድርገው መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግን አክብረው ለቃላቸው መገዛት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

መንግስት በዚህ ረገድ ህግ የማስከበሩን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በመጠቆም።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አደም ሙሳ በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መነሻው ፖለቲካና ፖለቲከኞች ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ነው የገለጹት።

የፖለቲካ ስብራቱን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከተቻለ ሌሎች ችግሮችን በቀላሉ እንደሚፈቱም ተናግረዋል።

በመሆኑም የውይይት መድረኩ ዋነኛ ግብ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳርን መፍጠር መሆኑን አብራርተዋል።

በዛሬው የምክክር መድረክ ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህና የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በታዛቢነት ተሳትፈዋል።

መድረኩ ቀጣይነት እንደሚኖረውም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም