ቀጥታ፡

የፀጥታ ኃይሉ ሰላምን የማስከበር ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል

ሀዋሳ ነሐሴ 16/2012 (ኢዜአ)  ዜጎች ያለስጋት ተንቀሳቅሰው  እንዲሰሩ የፀጥታ ኃይሉ ሠላምና ፀጥታን የማስከበር ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ሊወጣ እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ አሳሰቡ ፡፡ 

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሃድሶ ፕሮግራም ያሰለጠናቸው አንድ ሺህ 84 የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ዛሬ አስመርቋል ፡፡ 

በክልል መደራጀት ያስፈለገው ለፍትሐዊ ሀገራዊ ተሳትፎ ብሎም ያለውን ሀብትና መልካም አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ልማትን ለማምጣት እንደሆነ በምርቃው ስነሰርዓት ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።


አሁን ላይ የፖለቲካ ጥያቄያችን ምላሽ ያገኘ በመሆኑ ከፊታችን የልማትና መልካም አስተዳደር ትግል ይጠብቀናል ብለዋል፡፡

ኢንቨስትመንት የሚስፋፋው ብሎም ሁሉም ሰው   ሰርቶ ራሱንና ህዝቡን መጥቀም የሚችለው ሥጋት ሳይገባው መንቀሳቀስ ሲችል እንደሆነ አቶ ደስታ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተርድቶ ተግባሩን በቁርጠኝነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።


የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው በክልል በመደራጀታችን ልናሳካ ያቀድነውን ሁለንተናዊ ዕድገት ከግብ ልናደርስ የምንችለው ሀገር ስትረጋጋ በመሆኑ የፀጥታ ጉዳይ ላፍታ እንኳ የማንዘናጋበት ሥራ ነው ብለዋል ፡፡

ህዝብን  የሚያጋጩ አጀንዳዎችን አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላት በሲዳማ ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው እንደማይገባ አመልከተው ቢሮው የፀጥታ አካላትን በማስተባበር እነዚህን ለመታገልና በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሳፍንት ሙሉጌታ ዛሬ ለምረቃ የበቁት አንድ ሺህ 84 የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት የክልሉን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የሚያበቃ የአጭር ጊዜ የተሀድሶ ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የልዩ ኃይል አባላት በህዝብና በመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመረዳት ሁሉንም በእኩልነት ማገልገልና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል ኮንስታብል አቡቴ አርገታ በሰጡት አስተያየት  ከዚህ በፊት በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ውስጥ ሲገለገሉ መቆየታቸውንና ስልጠናው ተጨማሪ ዕውቀት እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ያገኘነውን የፀጥታ ማስከበር ልምድ ከወሰድነው ስልጠና ጋር በማዳበር  የህዝባችንን ደህንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ሌላው ተመራቂ ምክትል ሳጂን መንገሻ ቃሚሶ በበኩሉ በክልሉ ያሉ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ገልጿል ፡፡

በምረቃው ስነሰርዓት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሩ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኙ ሲሆን ለስልጠናው  መሳካት  አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላትም ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም