ቀጥታ፡

የተራቆተ መሬትን መልሶ በደን በመሸፈን  ወጣቶች ለገቢ ማስገኛ እንዲጠቀሙበት ተመቻቸ

ማይጨው ነሐሴ 16/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ደቡባዊ ዞን የተራቆተ መሬትን መልሶ በደን በመሸፈን ስነ ምህዳርን ከማስተካከል ባሻገር ወጣቶች ለገቢ ማስገኛ እንዲጠቀሙበት መመቻቸቱን የኢትዮጵያ የአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ።

በአሁኑ ወቅት በልማቱ አራት ሺህ ያህል ወጣቶች  የስራ እድል ማግኘት እንደቻሉም ተመልክቷል።

በኮሚሽኑ እንዳመኾኒ ወረዳ የደን ልማት ዘርፍ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዳኛው ካልአዩ ለኢዜአ እንደገለፁት ከኖርዌ እና ስዊድን መንግስታት ጋር በመተባባር በሁለት ወረዳዎች ተራቁቶ የነበረ የደን መሬት ልማት ሲካሄድ ቆይተዋል።

በእንዳመኾኒ እና ኦፍላ ወረዳዎች በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ላለፉት አምስት ዓመታት በተከናወነው የደን ልማት ስራ የአከባቢው ስነ ምህዳርን ከማስተካከል ባሻገር ለወጣቶች ለገቢ ማስገኛ እንዲጠቀሙበት መመቻቸቱን ተናግረዋል።


በቀበሌዎቹ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን 200ሺህ ችግኝ በመትከል ተራቆቶ የነበረው አንድ ሺህ 780 ሄክታር መሬት  ደን ማልበስ ተችሏል ብለዋል።

ከ15 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ደግሞ ከሰውና እንስሳ ንኪኪ ነጻ በማድረግ አከባቢው ወደ ቀድሞ ይዞታው መቀየሩን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ ለመፈጸም ባለፉት አምስት ዓመታት ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ውጤት በማምጣቱ ወደ ሌሎች አከባቢዎች ለማስፋት የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል።

መልሶ እንዲያገግም የተደረገው አከባቢ አራት ሺህ ያህል  ወጣቶቹ በንብ ማነብና ሌሎች የልማት ስራዎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በቀጣይ የደን ልማት ስራው በተቀናጀ መልኩ በነቅሰገ እና ኦፍላ ወረዳዎች ለመስራት ታቅዷል።


ተራቁቶ የነበረው አከባቢ  በደን እንዲሸፈን በማድረግ ረገድ ፕሮጀክቱ ውጤታማ ስራ መስራቱን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት አስተባባሪ አቶ ፍሰሀ ገብረኪዳን ናቸው።


በተለይም በእንዳመኾኒ ወረዳ  ተራቁቶ የነበረው ሰፊ መሬት ለጎርፍ አደጋ አጋላጭ ሆኖ  አሁን ላይ መልሶ በመልማቱ አካባቢው  አረንጓዴ ለብሶ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

በዚህ ወረዳ  የእምባሓዝቲ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሞላ አብርሃ በሰጠው አስተያየት ከሌሎች ወጣቶች ጋር በማህበር ተደራጅተው  ያለሙትን አምስት ሺህ ባህር ዛፍ አድጎ ለሽያጭ መድረሱን ተናግረዋል።

የደን ልማት ስራው በስራ ኣጥነት ምክንያት ይሰደድ የነበረው ወጣት ኣሁን ላይ በኣካባቢው ያለውን ሀብት እንዲመለከት ኣድርጎታል ብልዋል።

የቀበሌው አርሶአደር ተስፋዬ ገብሩ በበኩላቸው የተራቆተ መሬት በደን መሸፈኑ ከተራራው እየመጣ በማሳቸው  ጉዳት ያደርስብን ከነበረው ጎርፍ ስጋት ተላቀናል ብለዋል።


ከ20 አርሶአደሮች ጋር በመሆን ሰባት ሄክታር መሬት ላይ ባህርዛፍ በማልማት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የዞኑ አጠቃላይ የደን ሽፍን ከ157 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መሆኑን ከዞኑ አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም