ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት ሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ ይገባሉ - ኮርፖሬሽኑ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 16/2012 ( ኢዜአ) በግንባታ ላይ የነበሩት ሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአዲሱ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ባለፉት አስርት ዓመታት በአማካይ 10 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማሳየቱንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለዚህም ደግሞ በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ መጀመር እድገቱን በማፋጠን አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታመናል።

የፓርኮቹ መስፋፋት የከተሞችን እድገት በማፋጠን፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እንዲሁም የአገሪቱን ገፅታ በመቀየር ረገድ ድርሻው ቀላል አይደለም።

የወጪ ምርት በዓይነትና በብዛት እንዲያድግ፣ የውጭ ምንዛሪን በማሳደግ እንዲሁም የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካትና ለገቢ ምርት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረትም እንዲሁ።

ለተግባራዊነቱ መንግስት ፓርኮችን እያስፋፋ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገልጿል።

የኮርፖሬሽኑ የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደርቤ ደበሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ፓርኮቹን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመገንባት ላይ ይገኛል።

በአገሪቱ በአጠቃላይ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም ሰባቱ በስራ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሁሉም ፓርኮች ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

ከነዚህም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እየተገነባ ያለው ፓርክ በቅርቡ ወደ ስራ ከሚገቡት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁሉንም ፓርኮች በማጠናቀቅ ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ለማፋጠንና የቴክኖሎጂ ሽግግርንም ለማምጣት እንደሚሰራም ኃላፊው ገልጸዋል። 

ግንባታቸው የተጠናቀቁት የድሬዳዋ፣ የቂሊንጦ፣ የቦሌ ለሚ 2ና የአይ ሲ ቲ ፓርኮች ናቸው።

እንዲሁም በሁመራ፣ በአሶሳና በአይሻ ፓርኮች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በፓርኮቹ  የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለአሜሪካና ለአውሮፓ ገበያ ታቀርባለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም