ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥ መመለሻው ቢደርስም በእድሳት እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2012 (ኢዜአ) ለህዳሴ ግድብ ቦንድ የገዙ ዜጎች የመመለሻ ጊዜው ቢደርስም በእድሳት ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ ፡፡

የግድቡ ግንባታ ከጅማሮው እስካሁን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ስኬት የቻሉትን ሁሉ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በርካቶች ቦንድ በመግዛት ድጋፍና አጋርነታቸውን በማሳየታቸው ግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ላይ የደረሰ ሲሆን ለፍፃሜ ለማብቃትም ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በመሆኑም ቀደም ሲል ቦንድ ገዝተው የነበሩ ዜጎች የቦንዱ መመለሻ ጊዜ ቢደርስም ወለዱን ጨምሮ ዳግም ቦንድ እየገዙ ድጋፋቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ተገልጿል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም እንደገለጹት፤ የድጋፍ ማሰባሰቡ ሂደት እንደቀጠለ ነው።

ከዚህ ቀደም ቦንድ የገዙ ሰዎች ዳግም ቦንድ ሲገዙና ሲያድሱ ለግድቡ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፈጠራቸው መልካም አጋጣሚዎችና ሁነቶች መካከል አንዱ የቁጠባ ባህልን ማሳደግ እንደሆነ ገልጸው፤ የቦንድ ግዥው የአገርን የኢኮኖሚ እድገት በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም