ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኪነ ጥበብ ሰዎች መነፅር ሲገለጥ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኪነ ጥበብ ሰዎች መነፅር ሲገለጥ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኪነ ጥበብ
ሰዎች መነፅር ሲገለጥ::
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ የሲቪል ስራው 88 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ክንውን ደግሞ 46 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።
የኮርቻ ግድብ (ሳድል ዳም) ተብሎ የሚጠራውም የግንባታ ክንው 99 በመቶ መድረሱ ተረጋግጧል።
የግድቡ ግንባታ በስኬት እየተካነወነ ሲሆን በሶስቱ ተፋሰስ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን) መካከል የሚካሄደው ድርድርም ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያውያን አርቲስቶች የዘመናት ቁጭት ዛሬ ላይ ተስፋ አሳድሮ የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት ላይ ደርሷል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው ዓባይን ሲያወድሱ፣ ሲያሞካሹና ሲወቅሱ የነበረበት ዘመን አልፎ ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል።
ባለፈው ወር በግድቡ በተያዘው 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ''ዓባይ'' ለአገሩ ልማት መዋል መጀመሩ ቅኝትና ዜማን አስለውጧል።
''እንጉርጎሮ ይብቃ'' ብለው የዘፈኑትን ወጣት አርቲስቶችንም ዓባይ ሰምቶ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ''በቅቷል'' ብሏቸዋል።
ሁሌም ያለውን ማካፈልን፤ የጎደለ መሙላትንና የጋራ ተጠቃሚነትን የማይዘነጋው ኢትዮጵያዊ ባህልና ማንነት በኪነ ጥበብ ሥራዎቹ ተዘንግተው አያውቁም። በኃይልና በጉልበት ለሚመጡበት ደግሞ ''አትንኩኝ'' ማለትንም ሥራዎቹ ያንፀባርቃሉ።
ሰሞኑን ለሕዝብ ዓይንና ጆሮ የቀረቡት በሙዚቃው ዘርፍ የወጡ ሥራዎችም ይህንኑ የሚያንጸባርቁ ናቸው። ትውልዱ አኩሪ ታሪኩን እየጻፈና አገሩን በልማት ወደ ፊት የሚያራምድ ተግባር እያከናወነ መሆኑን አንጸባርቀዋል።
ታዋቂው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ''ደሞ በዓባይ'' ብሎ በመሰየም ከሁለት ሳምንት በፊት የለቀቀው አልበም ይህንኑ ስሜት አጉልቶ አሳይቷል።
ዓባይ ለሁሉም የሚበቃ መሆኑንም አሳይቶበታል። በሌላ መንገድ የሚመጡ ካሉ ደግሞ 'ከሞከሩን'' በማለት እንደማያወጣ አንጎራጉሯል።
የእንግሊዝ ዜና ማሰራጫ ድርጅት (ቢቢሲ) ባሰራጨው ዘገባ እንዳመለከተው የዘፈኑ ግጥም በእንግሊዝኛ፣ በዓረብኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ መልዕክቱን በውጭ ለሚገኙ በተለይም ለግብፅና ሱዳን ሕዝብ እንዲደርስ ተደርጓል።
በዩ ቲዩብ ላይ የተጫነው የቴዲን ሥራ በ24 ሰዓት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደተመለከቱትም በዘገባው ቢቢሲ አስፍሯል።
የአርቲስቱ ስራ ይህ ፅሁፍ አስከተዘጋጀበት ድረስ ደግሞ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች አልበሙን ተከታትለውታል።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን #ግድቡ የኔ ነው ብለው በጀመሩት ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ከግድቡ ድርድር በላይ፤ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው የሚፈልጉ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለመቋቋም እየሰሩ ናቸው ሲልም የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በተጨማሪም ወጣቱ ድምፃዊ ዘሩባቤል ሞላ ''ኢትዮጵያ'' የተባለው አልበሙ የአገሩን ብሩህ ተስፋ በግድቡ ግንባታ ምስል አስደግፎ አንጸባርቋል ብሏል።
መቅደስ አበበና ታደሰ መከተ ያወጡት ''የትንቢት ቃል'' የተሰኘ አልበማቸውም የአገራቸውን ከፍታ ያሳየና የኢትዮጵያ ሕዝብም ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናከር ያሳስባል ይላል የቢቢሲ ዘገባ።
''አመፀኛ ውሃ'' በሚል ርዕስ የወጣው የቴዎድሮስ ሞሲሳ አልበምም በዚሁ ግድብ ዙሪያ የተቀነቀነ ሥራ ነው።
አልበሙ ዓባይ ለአገሩ ልማት ሳይውል፤ ሌሎችን ሲጠቅም መኖሩን በመውቀስ ዛሬ ለአገሩ ልማት መዋሉ የዘመናት እንቆቅልሽ መፈታቱን ያበስራል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከብዙ የኪነ ጥበብ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ የተመለከቱበት የጥበብ መነፅር እንዲህ ተቃኝቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በዚህ ሳምንት በግድቡ ግንባታ ክንውንና የወደፊት አቅጣጫ ላይ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ''ያቀድነውን መፈጸም እንደምንችል ለኛም ለወዳጆቻችን ጨምሮ ለሚጠራጠሩንም ያሳየንበት ድል ነው'' ማለታቸው ይታወሳል።
ግድቡ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን፤ የነፃነት ዓርማ መሆኑን አመልክተው፤ ኢትየጵያ በአፍሪካ ነፃ የሆነች አገር ብቻ ሳይሆን፤ ነፃ ሆና የምትቀጥል አገር መሆኗን እንዳሳየችበት ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም "ግድቡ ከውሃ ሙሊት ተሻግሮ ወደ ሃይል ማመንጨት ስራ እየተንደረደረ በመሆኑ የተያዘው በጀት ዓመት ወሳኝ ጊዜ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
"እኛ ኢትዮጵያውያን ስናብር ምን ማሳካት እንደምንችል፤ ስንለያይ ደግሞ ምን እንደሚገጥመን ያሳፍነባቸው የታሪክ ሂደቶች አሳይተውናል" ሲሉም በግድቡ ላይ የህዝቡን ጠንካራ ተሳትፎ አሞካሽተዋል።
የግድቡ የውሃ ሙሌት ከተከናወነ ወዲህ ሕዝቡ 116 ሚሊዮን ብር ለግንባታው ማዋጣቱን የግንባታው ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ አስታውቋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶች ተጀምረዋል።