የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በዛሬው እለት ከ1 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በዛሬው እለት ከ1 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከለ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በሀገር ውስጥ ካሉ የዳያሥፖራ ማህበራት ጋር በመሆን በዛሬው እለት ከ1 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከሉ፡፡
ችግኞቹ የተተከሉት በአዲስ አበባ ቦሌ ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት ኤጀንሲው ከአምና ጀምሮ በአረንጓዴ አሻራው ላይ ሲሳተፍ ቆይቷል።
የተተኩሉ ችግኞን በማህበር በተደራጁ ወጣቶች ለ18 ወራት ተንከባክበው እንዲያጸድቁ በስመምነት ላይ ደርሰው ስራውን ማስጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዳያሥፖራው ባለበት ሆኖ የአባይን ተፋሰስ እንዲያለማ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በዛሬው ዕለትም ከ1 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው በተለይ ዳያሥፖራውን በሃገሩ ጉዳይ ላይ ካለበት ሆኖ በሚችለው ሁሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ዳያሥፖራው ከዚህ ቀደም በህዳሴ ግድብ፣ ኮሮናን በመከላከል ስራ እና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደተሳተፈው ሁሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅረበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዳያሥፖራ ማህበር ሰብሳቢ አርቲሰት ዘለቀ ገሠሠ በበኩሉ ማህበራቸው የተተከሉ ችግኞች ወጣቶች እንዲንከባከቡ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደረጉ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የኦሮሚያ ዳያሥፖራ ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ ሞሣ ሼኮ እንዳሉትም ማህበራቸው በተያዩ ጊዜያት በችግኝ ተካለ መርሃ ግብር ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በውጭ ሀገራት ከሚገኙ 12 ሺህ አባሎቻቸው ጋር በዚህ ዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንም ጠቅሰዋል።
በዳያሥፖራው ማህበረሰብ የተተከሉትን ችግኞች ለመንከባከብ የስራ እድል ያገኙት ወጣቶችም መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮው አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ (አረንጓዴ አሻራ) መርሃ ግብር ለመትከል የታሰበውን 5 ቢሊዮን ችግኞችን ማሳካት መቻሉ ይታወቃል።