ቀጥታ፡

በጤና ማህበራት የተዘጋጀው አገር አቀፍ የኮሮና ቫይረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ተጀመረ

አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2012 (ኢዜአ) በአገሪቱ በሚገኙ 11 የጤና ሙያ ማህበራት የሚተገበረው አገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ የኮሮና ቫይረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀመረ።

መርሃ ግብሩ በተለይም በበዓላት ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን መዘናጋት ማስቆም፣ በኮቪድ-19 ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግና በአተገባበር ላይ ትኩረት ለመስጠት መዘጋጀቱ ተገልጿል።

መረሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት ኮቪድ-19 መከሰቱን ተከትሎ መከላከልን መሰረት ያደረጉ ተግባራት በሚኒስቴሩና በጤና ባለሙያዎች በስፋት እየተካሄዱ ነው።

ይሁን እንጂ  በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋትና  የአተገባበር ክፍተት ለስርጭቱ መስፋፋት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል ብለዋል።

በዚህም የስርጭቱ ምጣኔ ከፍ ያለበት ወቅት ላይ መደረሱ ችግሩን አሳሳቢ  እንዳደረገው ገልጸዋል።

ይህም የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ጫና ውስጥ በመክተት በጤናው ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲስተጓጎል ምክንያት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል።

በዋነኝነትም በበዓላት ወቅት የሚፈጠር የህዝብ ጥግግትና ግርግር ለስርጭቱ መስፋፋት አንዱ ምክንያት እንደሚሆን ተናግረዋል።

በዚህ ወር የተጀመረው'' የማንም'' የምርመራ ዘመቻ የቫይረሱን የስርጭት መጠን አመላክቷል ያሉት ወይዘሮ ሳህርላ፣ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን በማካሄድ ህብረተሰቡን መታደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት የሚሰሩ የጤና ሙያ ማህበራት በበጎ ፈቃድ ከዛሬ ጀምሮ በመላ አገሪቱ በመዘዋወር ከክልል ጤና ቢሮዎችና ጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ግንዛቤ  እንደሚያስጨብጡ አስታውቀዋል።

መርሃ ግብሩን ያስተባበረው የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር  ፕሬዝዳንት አቶ ዘነበ አካል በበኩላቸው ማህበራቱ ተቀናጅተው በየአመቱ በበጎ ፈቃደኝነት ህብረተሰቡን እንደሚያገለግሉ አስታውቀው፣ ዘንድሮ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከል እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

ይህም  የጤና ባለሙያዎች  ወረርሽኙን ህዝቡን በስፋት እያጠቃ ካለበት ሁኔታ  ለማውጣት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት ይሆናል ብለዋል።

በተለይም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም፣ርቀትን መጠበቅና የእጅ ንጽህናን መጠበቅ በህብረተሰቡ ዘንድ እየተዘነጉ መምጣታቸውን አስታውሰዋል።

ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች፣የትራንስፖርት መስጫ አካባቢዎች፣የገበያ ማዕከላትና ሌሎች ቦታዎች ላይ የጤና ባለሙያዎች በመዘዋወር ግንዛቤ እንደሚሰጡ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ባለሙያዎቹ ወቅቱ የበዓል መዳረሻ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መዘናጋትንና በግብይት ወቅት የሚኖረው ጥግግት ስርጭቱን እንደሚያስፋፋው በመገመት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት ይሰራሉ ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫዎች በመሰማራት እንቅስቃሴ መጀመሩንና በቀጣይ በመላ አገሪቱ እንደሚከናወንም  አመልክተዋል።

ይህም የጤና ባለሙያዎች ህዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል የገቡትን ቃል በተግባር እንደሚያሳዩ አቶ ዘነበ አስረድተዋል።

መርሃ ግብሩ እስከ መስከረም 30/2013 በመጀመሪያ ዙር በመላ አገሪቱ እንደሚካሄድ ታውቋል።

በቀጣይም የክልሎችንና የከተሞቹ ወቅታዊ ሁኔታን በማገናዘብ ሁለተኛው ዙር እስከ ታህሳስ 30/2013 እንደሚቀጥልም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም