ቀጥታ፡

በአዳሚ ቱሉ ወረዳ 25 ኩንታል አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዳማ ነሐሴ 16/2012 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ ወይሶ ቀንጨራ ቀበሌ 25 ኩንታል አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ። 

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ ዕጹ  በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት ሌሊት አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ ነው።

የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 -76201 አ.አ  አይሱዙ መኪና ተጭኖ ከሻሻመኔ ወደ መሀል ሀገር  ለማለፍ ሲሞክር በልዩ ኃይል አባላትና በመደበኛ ፖሊስ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።

አደንዛዥ ዕፁን 64 ኩንታል ከሰል በላዩ ላይ ተጭኖ ለማሳለፍ ሲሞክር በወረዳው በቅኝት ላይ በነበሩ አካላት ማግኘት እንደተቻለ  አመላክተዋል።

አሽከርካሪው መኪናውን   በማቆም ለጊዜው ቢሰወርም ለመያዝ ክትትል እየተደረገ  ኮማንደር አስቻለው አስረድተዋል።

"የአደንዛዥ ዕፅ የተሻለ ዋጋ ያስገኛል በሚል አርሶ አደሩ እንዲያመርት እየተደረገ ነው "ያሉት ኮማንደር አስቻለው፤ ለህብረተሰብ ጤና ጠንቅ የሆነው ማንኛውንም ዓይነት ተክል ለምቶ ከተገኘ ህብረተሰቡ አጋልጦ ለህግ አስከባዎች እንዲጠቁም መልዕክታቸወን አሰተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም