ቀጥታ፡

በአገራዊ መግባባት ላይ ፖለቲከኞች እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ  የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ መግባባት ላይ  እየተወያዩ ነው ፡፡
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክሩ የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት ልዩነቶችን በመገዳደልና በጥላቻ ስብከት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር የመፍታት ባህል ማዳበር ተገቢ ነው ብለዋል።

መድረኩም በፖለቲከኞች መካከል ያሉ ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ዓላማ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው ወደፊትም ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

"ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን የከዳ ፖለቲከኛ ነገ ቆምኩለት የሚለውን ብሔር እንዳማይከዳ ዋስትና የለም" ብለዋል አቶ ሙሳ በንግግራቸው።

ችግሮች ቢኖሩም እንኳን አገርን በመክዳት ሳይሆን በአገር ውስጥ ታግሎ ማስተካከል መልመድ ይገባል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በመድረኩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ በታዛቢነት ታድመዋል።

ዛሬ ማለዳ የተጀመረው የፖለቲከኞቹ ውይይት ከሰአት በኋላም እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም