ኢዜማ ሲያከናውናቸው በነበሩ ጉዳዮች ዙሪያ ግምገማ በማካሄድ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ ሲያከናውናቸው በነበሩ ጉዳዮች ዙሪያ ግምገማ በማካሄድ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀመጠ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሲያከናውናቸው በነበሩ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀናት ድርጅታዊ ግምገማ በማካሄድ ቀጣይ አገራዊ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወቀ፡፡
ኢዜማ ይህን ያስታወቀው ዛሬ በአዲስ አበባ ለጋዜጠኞችና ሚዲያ አካላት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
ኢዜማ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል፡፡
የኢዜማ ብሔራዊ ስራአስፈጻሚ አባልና የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ወርቅነህ እንዳሉት "ከፓርቲ ግብ አንጻር አገሪቱ ያሉባትን ችግሮች ለመቅረፍ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን እና ከፓርቲው ደጋፊዎች፣ ምሁራንና ሌሎች አካላት የሚነሱ ትችቶች ለመፈተሽ ግምገማው አስፈላጊ ነበር" ብለዋል፡፡
በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ከፓርቲው ፍፁም ገለልተኝ የሆኑ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ በመከታተል የሚታወቁ የፖለቲካ ተንታኞች የቀረቡ የመነሻ ጹህፎች ለውይይት ቀርበው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵን የለውጥ ሂደት እና አሁን ያለችበት ሁኔታ፣ አገራዊ ጉዳዩች፣ የለውጡ የሽግግር ሂደት፣ ምርጫን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ የሚሉት ከተጋባዥ እንግዶቹ የተነሱ ሃሳቦች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በአገራዊ አንድነት፣ በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና ዜጎች ደህንነት ዙሪያ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት ፓርቲው ኮሚቴ ማቋቋሙንም አስረድተዋል፡፡
የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ እንዳሉትም "ግምገማው የኢዜማን የእቅድ ክንውን ከመዳሰስ ባለፈ ፓርቲውን በሚመለከት ከአመራርና አባላት ምን አይነት እይታ እንዳለ በመፈተሽ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመከናወን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከስምምነት ተደርሷል" ብለዋል፡፡
ኢዜማ በአገራዊና ሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመው ኑ አብረን እንስራ ሲሉም ለሌሎች ፓርቲዎች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ በበኩላቸውም ፓርቲያቸው በዴሞክራሲያዊ፣ አገራዊ አንድነት እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ከሌሎች የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ የፓርቲው ስትራቴጂክ ግብ፣ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ የለውጡ ጉዞምን ይመስላል፣ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን መምሰልና መሆን አለበት፣ የፓርቲዎች ቁመና እና የሚነሱ ችግሮች በምን መልኩ ይፈቱ የሚሉት ጉዳዮች በብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ የተሰጠባቸው አጀንዳዎች እንደነበሩ ኢዜማ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል፡፡
አገራዊ አንድነትና ሰላምና መረጋጋት፣ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም አስተምህሮ እንዲሁም እርሱን ከሚመስሉ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውህደት መፈጸም በቀጣይ በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን አስታውቋል።
ኢዜማ አደረኩት ባለው ግምገማ የነበሩበትን ድክመቶችና ጠንካራ ጎኖች በመለየት በቀጣይ ለሚደረገው አገራዊ ምርጫ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጾ በሁሉም አደረጃጀት የፓርቲው እንቅስቃሴ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የፖሊሲ አማራጭ በማቅረብ እና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ዜጎች በተለይ የኢዜማ አባላት በአካባቢያቸውን ሠላም እና ደህንነት በማስጠበቅ ከሁሉም አካላት ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል፡፡