በጎንደር ለችግር ለተጋለጡ 10ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ለችግር ለተጋለጡ 10ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ
ጎንደር፣ ነሐሴ 15/2012 (ኦዜአ) በጎንደር ከተማ በኮሮና ወረርሽ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ 10ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች የምግብና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ፡፡
በግብረ ኃይሉ የሃብት ስርጭት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተቀባ ደሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉን ያደረጉት በተገባደደው ሳምንት የተለያዩ ቀናት ውስጥ ነው።
በዚህም በጎንደር ስድስት ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ 10ሺህ ለሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በነፍስ ወከፍ 10 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ቀደም ሲልም 3ሺህ 700 ለሚጠጉ ችግረኛ የህብረሰብ ክፍሎች ዱቄትና የምግብ ዘይት ማሰራጨቱን አውስተዋል።
"ወረርሽኙ መከሰቱ ከተሰማ ማግስት ጀምሮ በቀን ስራ እየተዳደርኩ የማገኘው ገቢ በመቀዛቀዙ ችግር ላይ ወድቄ እገኛለሁ" ያሉት የፋሲል ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አደራጀው ሲሳይ ናቸው፡፡
በሳምንቱ ከተማ አስተዳደሩ 10 ኪሎ ግራም ዱቄት ያደረገላቸው ወርሃዊ ድጋፍ ኑሮቸውን ለመደጎም እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
ወይዘሮ ታድላ አባተ በበኩላቸው በቀን ስራ በሰው ቤት ልብስ በማጠብ እየተዳደሩ እያለ አሰሪዎቻቸው በሽታውን በመፍራት ስራውን አቋርጠውባቸው ገቢ በማጣት መቸገራቸውን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ በሰጣቸው የዳቦ ዱቄት ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል ቢረዳቸውን እገዛው እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማው ባለፉት አምስት ወራት ለህብረተሰቡና ባለሀብቶች 12 ሚሊዮን ብር በዓይነትና ጥሬ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ግብረ ኃይሉ አመልክቷል፡፡