በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ወጥና የተናበበ የፋይናንስ ሥርዓት ይዘረጋል --- የገንዘብ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ወጥና የተናበበ የፋይናንስ ሥርዓት ይዘረጋል --- የገንዘብ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ወጥና የተናበበ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ይደረጋል ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ (ኤ.ኤ.ቢ.ኢ) ጋር በመሆን በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት (አይ.ኤፍ.አር.ኤስ) ፍኖተ ካርታ አስመልከቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ እንደገለጹት፣ የአገሪቷን የፋይናንስ ኩባንያዎች ሒሳብ አያያዝ የሚያሻሽል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ፍኖተ ካርታ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቷል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቷ ሲተገበር ቢቆይም እምብዛም ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱንም ገልጸዋል።
ይህም በመሆኑ አሠራሩን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ በአዲስ መልክ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ማስፈለጉንም ጠቅሰዋል።
አሠራሩን መተግበሩ ጥቅሙ ለኩባንያዎች ብቻ አለመሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ለአገሪቷም የተሻለ የታክስና የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዳይሬክተር ጀነራል ወይዘሮ ሂክመት አብደላ "አዲስ የተከለሰው ፍኖተ ካርታ ብዙ ነገሮችን ያሻሽላል" ብለዋል።
በአዲሱ ፍኖተ ካርታ ሙሉ ደረጃዎችን ያሟላ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸው ከፍተኛ የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው ኩባንያዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
እንደ ወይዘሮ ሂክመት ገለጻ ሙሉ ደረጃዎችን ያሟላ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት እንዲተገብሩ የሚጠበቅባቸው ኩባንያዎች ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የአክሲዮን ኩባንያዎችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ናቸው።
በተጨማሪም በመንግሥት ቁጥጥር የሚደረግበት የጡረታ የፕሮቪደንት ፈንድ፣ የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ የሸማች ማኅበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ይገኙበታል።
በገንዘብ ደረጃም ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ፣ ጠቅላላ ንብረታቸው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ፣ ጠቅላላ ዕዳ ከ200 ሚሊዮን በላይና የሠራተኛ ቁጥራቸው ከሁለት መቶ በላይ መሆን አለበት።
"ከላይ ከተጠቀሱት አራቱ መስፈርቶች ሁለቱን አሟልቶ የተገኘ ኩባንያ የተሟላ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል" ብለዋል።
በተመሣሣይ አነስተኛ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸው ደግሞ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ20 እስከ 300 ሚሊዮን ብር የሆኑ መሆናቸውን ወይዘሮ ሂክመት አመልክተዋል።
"ጠቅላላ ሀብታቸው ከ20 እስከ 200 ሚሊዮን ብር፣ ጠቅላላ ዕዳ ከ20 እስከ 200 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የሠራተኛ ቁጥር ከ20 እስከ 200 የሆኑ ኩባንያዎች እዚህ ይመደባሉ" ብለዋል።
በዚህ ረድፍም ከአራቱ ሁለቱን መስፈርት አሟልቶ የተገኘ ኩባንያ አነስተኛና መካከለኛ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት እንደሚተገብሩ ገልጸዋል።
አሠራሩን የጀመሩ ኩባንያዎች እስከ ሦስት ዓመት ጊዜ የተሰጣቸው ሲሆን፣ እስካሁን ላልጀመሩት ደግሞ አራት ዓመት ጊዜ እንደተሰጣቸውም ወይዘሮ ሂክመት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የካፒታል ገበያን ለመቀላቀል እየሠራች በመሆኑ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት መተግበሩ ለኩባንያዎች ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።