በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው --- የገንዘብ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው --- የገንዘብ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ወቅታዊ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ አስመልከተው ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል "ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መዛኝ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውደቀት እያሳየ የሚሄድ ነው የሚል ትንበያ ያወጣሉ።" የሚለው አንዱ ነበር።
ለዚህ ደግሞ የኢኮኖሚ መዛኞቹ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባት አገር መሆኗ፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችቷም አናሳ መሆኑን በማሳያነት ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ኢኮኖሚው የተናቃቃ ነው ይላል። ይህ እንዴት አብሮ ይሄዳል? ተብለው ተጠይቀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ የኢኮኖሚ መዛኞቹ ''የብዙ ደሀ አገራት ዕዳ ይሰረዝልን የሚለውን ጥያቄ መሠረት አድርገው የሰሩት ነው እንጂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተነቃቃ ነው'' ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካበድ ሊባል የሚችል ብድር ከግሉ ዘርፍ አለመበደሯን አስታውሰው፣ "መንግሥት በቀጣይ በአጭር ጊዜ የሚመለሱና ከፍተኛ ወለድ ያላቸውን ብድሮች ለመውሰድ አያስብም" ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተከማቸ ብድር እየከፈለ መሆኑን ሲገልጹም "ለመንገድ መሠረተ ልማት ተብሎ ተውስዶ የተከማቸ ስድስት ቢሊዮን ብር መከፈሉንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቀሴ መኖሩን የገለጹት ዶክተር እዮብ፣ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረው ኢኮኖሚው በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ለዶክተር እዮብ ሌላው ከመገናኛ ብዙሃን የቀረበላቸው ጥያቄ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደግል የማዞሩ ጉዳይ በግልጽ ምን ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚል ነው።
ሚኒስትር ዴኤታው ይህንንም ሲመልሱ "ሂደቱ በተሻለ መልክ እየሄደ በመሆኑ ምንም ብዥታ የለም" ብለዋል።
በተለይ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተያይዞ የሚነሳው አጠቃላይ ሁኔታውን ካለመረዳት ነው እንጂ ነገሮች በጥሩ መልኩ እየሄዱ ነውም ብለዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ግሽበትና በኢኮኖሚው ላይ እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቀነስ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ምን እየተሰራ እንደሆንም ተጠይቀዋል።
በዚህም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት የምግብና የፍጆታ ዕቃዎችን ከታክስ ነፃ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታውሰው ሌሎች ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ አበዳሪ ተቋማት ይበደሩ መባሉ ሊያስከትል የሚችለው ዘላቂ ጉዳት ምን እንደሆና የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሽከርካሪ አጠቃቀምን የተመለከተም ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ከጅምሩ ባንኮቹ መክፈል የሚችሉትን ያህል ብቻ የሚበደሩ በመሆኑና አስፋላጊው ጥንቃቄ ስለሚደረግ ጉዳት እንደሌለው ገልጸዋል።
"የመንግሥት ተሽከርካሪዎች አጠቃቀምን አስመልክቶ የወጣው መመሪያም የተሽከርካሪ አቅርቦቱና ፍላጎቱ የተጣጣመ ባለመሆኑ የሚከለስ ይሆናል" ብለዋል።