ቀጥታ፡

ዶክተር ሣሙዔል ኡርቃቶ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ቦታን ተረከቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማሪያም አዲስ ለተኳቸው ዶክተር ሣሙዔል ኡርቃቶ የሥራ ርክክብ አደረጉ።

በሥራ ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።  

ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማሪያም ላለፉት ሁለት ዓመታት ሚኒስቴሩን ለማቋቋም የሚያግዙ በርካታ ሥራዎችን ማከናወናቸው በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።  

ለአብነትም በዘርፉ ውጤት እንደሚገኝባቸው የታመነባቸው አዋጆችና አሰራሮች እንዲዘረጉ እንዲሁም የቋንቋ ፖለሲ እንዲዘጋጅ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።   

በቴክኒክና ሙያ ዘርፍም ከልማት አጋሮችና ተቋማት ሀብት በማሰባሰብ ዘርፉ እንዲጠናከር ሚናቸውን ተወጥተዋል።

በቀጣይ ዓመት የሚተገበረው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት በስኬት እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውም በመድረኩ ተብራርቷል።   

ከዚህ ባሻገር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አጋጥሞ የነበረው አለመረጋጋት መቋጫ እንዲያገኝ በሳል አመራር መስጠታቸውም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።   

ፕሮፌሰር ሒሩት በበኩላቸው "ሚኒስቴሩ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የበኩሌን ጥረት አድርጌአለሁ፤ ከጥንስሱ ጀምሮ በመሳተፌም ዕድለኛ ነኝ'' ሲሉም ተደምጠዋል።    

በጋራና በትብብር መሥራት ለስኬት ቁልፍ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ሒሩት ለሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት ምሥጋና አቅርበዋል።    

በሚኒስቴሩ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች የበለጠ እንደሚስፋፉ እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው ለዚህም አዲስ በተሾሙበት ቦታም ሆነው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

በቅርቡ አዲስ የተሾሙት የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሣሙዔል ኡርቃቶ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብልፅግና የሚረጋገጠው በዕውቀት መሆኑን ጠቁመው፣ "ዘርፉን ለመምራት ዕድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።  

ለዚህም መልካም ውጤቶችን በማስቀጠል የሚሻሻልና የሚጎድለውን ለመሙላት ዝግጁ እንደሆኑ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዜጎችን በብቃትና በጥረት አሰልጥነው እንዲያፈሩ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በሰጡት ሹመት ፕሮፌሰር ሒሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ እና ዶክተር ሣሙዔል ኡርቃቶን ደግሞ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም