የ"ሳፋየር " ማዕድን ለመንግሥትና ወጣቶች የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ነው

አክሱም፣ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የተገኘው የ"ሳፋየር" ማዕድን ለወጣቶች የሥራ ዕድልና ለመንግሥት የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን የዞኑ የማዕድንና ኢነርጂ መሥሪያ ቤት ገለጸ።

በመሥሪያ ቤቱ የማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ፍትዊ ወልዱ ለኢዜአ እንደተናገሩት በጭላና ላዕላይ ማይጨው ወረዳዎች ከሁለት ዓመት በፊት የ"ሳፋየር" የከበረ ማዕድን እምቅ ሀብት መኖሩን በጥናት ተረጋግጧል።

ለጌጣጌጥ አገልግሎት የሚውለው ማዕድኑ ለወጣቶችና አርሶ አደሮች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።

የማዕድኑ የጥራት መለኪያ መሣሪያ ባለመኖሩ፣ ለሀገሪቱና ክልሉ አካባቢም አዲስ በመሆኑ ገበያ ላይ ጎልቶ ባይወጣም አሁን ባለው የመሸጫ ዋጋ አንድ ግራም ''ሳፋየር'' እስከ 50 ሺህ ብር እየተገበያየ ነው ብለዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የ132 ኪሎ ግራም ሳፋየር በባህላዊ መንገድ ተመርቶ ፍቃድ ባላቸው የማዕድን ምርት ንግድ ላይ በተሰማሩ አካላት አማካኝነት ወደ ውጭ በመላክ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘቱን አስረድተዋል።

ማዕድኑ እንደ ወርቅ ግብይት የሚካሄድበት አሰራር ባለመዘርጋቱ በሕገወጥ አምራቾችና አዛዋዋሪዎች የሚባክንበት አጋጣሚ እንዳለም ተመልክቷል።

የማዕድን ሀብት አሰራርና አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ፣ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው አካላት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ በማመቻቸት ሕገወጥነትን ለመከላከል ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል።

በሁለቱም ወረዳዎች በባህላዊ መንገድ ''ሳፋየር'' በማምረት የተሰማሩ 39 የወጣቶች ማኅበራትና 227  ፍቃድ ያላቸው የማዕድን አዘዋዋሪዎች እንደሉም ከአስተባባሪው ገለጻ መረዳት ተችሏል።

በአክሱም ከተማ ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው የማዕድኑ ንግድ ሥራ  ከተሰማሩት መካከል  አቶ ዳንኤል አስፋው እንዳሉት ዘርፉ በትኩረት ከተሰራበት ለሀገሪቱ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ይሆናል።

የሳፋየር ማዕድኑ የጥራት ደረጃው በዕይታ በመለየት ከአምራቾቹ  ከ20 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ባለው ዋጋ እንደሚረከቧቸው ተናግረዋል።

ከአምራቾች እየገዙ በሕግ አግባብ ወደ ውጭ እየላኩ ከሚያገኙት ገቢ ለመንግሥት ግብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሕገወጥ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች በመበራከታቸው መንግሥት ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በጭላ ወረዳ የጭላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ተሻለ ፍስሐ  በበኩሉ 15 አባላት ያሉት ማኅበር አቋቋሙው በሳፋየር ማምረት ሥራ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግሯል።

ማኅበሩ ሰባት ግራም ሳፋየር እንዳገኙ እና ሕጋዊ ፈቃድ ላላቸው ነጋዴዎች ግራሙን  በ20 ሺህ ብር ሂሳብ  እንደሚሸጡ ጠቅሷል።

በዚሁ ወረዳ የማይኮሆ አካባቢ ነዋሪ ወጣት ሲሣይ ለአከ ማዕድኑ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዋነኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።

"ወደ ስደት ያመራ የነበረው ወጣት ተደራጅቶ ሳፋየር በማምረት ተጠምዷል፤  በጭላ ከተማ መኪናና ሞተር የገዙና ቤት የሰሩ በርካታ ወጣቶች አሉ፤ እኔም በዚሁ ሥራ ተሰማርቼ ባገኘሁት ገቢ  ሞተር ሳይክል ገዝቼያለሁ" ብሏል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን  በወርቅ፣ ሳፋየር እና ለግንባታ አገልግሎት በሚውሉ ማዕድናት ማምረት  ከ7 ሺህ 100 በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም