ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የትብብር ተምሳሌት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

አዲስ አበባ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) - "ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስንተባበር ምን ማሳካት አንደምንችል ያስተማረ ፕሮጀክት ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

አሁን ላይ ግድቡ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ በመሆኑ ዜጎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት አባላት በዛሬው ዕለት የምክር ቤት ጽሕፈት ቤቱን የ2012 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጻምና የ2013 ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።

ሪፖርቱ ከዚህ ቀደም ለምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ይታወሳል።

በዛሬው መድረክ በ2012 በጀት ዓመት በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢ ሥራዎች አማካኝነት ለግድቡ ከ744 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንና በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል።

በተጨማሪም የግድቡ አሁናዊ ክዋኔ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት ቀርቦላቸዋል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢኒጂነር ስለሺ በቀለ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ የስቪል ሥራው 88 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው 46 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የኮርቻ ግድብ ሥራ ደግሞ 99 በመቶ መከናወኑን ጠቁመው በዩኒት ዘጠኝና አሥር የተርባይን ተከላ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የበጋ ወቀት ግድቡን ወደ 595 ሜትር ለማድረስ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የተጠቀሰው ወቅት የ11 ተርባይኖች ገጠማ እንደሚጠናቀቅና በክረምቱ ውቅት ደግሞ ግድቡ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚይዝም አብራርተዋል።

በመሆኑም እያንዳንዷ ቀን ሳትባክን ሥራው በጥንቃቄ በመሠራት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ለግድቡ 121 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መውጣቱን ጠቁመው ግድቡን ለማጠናቅቅም የሚፈጀው አጠቃላይ ወጭ 160 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም በተለይ የሕዝባዊ ተሳትፎ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሀሳብ አንስተዋል።

የገንዘብ ማሰባሰቡ ረገድ ከተለመደው አሰራር ወጣ ብሎ አዳዲስ ሥልቶች እንዲቀየስም ጠይቀዋል።

በዚህ ረገድ የክልሎች ተሳትፎ እጅግ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አባላቱ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ግድቡ የአንድ አካል የበላይነትን አስቀርቶ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያሰፈነ በመሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ እየተቸረው ነው ብለዋል።

በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ፍትሐዊ አቋም በማንጸባረቅ ረገድ በስፋት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዓረቡ ዓለም ጋር የፈጠረችውን ዘመናትን የተሻገረ የንግድ ትሥሥር በመጠቀም ስለግድቡ ያለውን የተዛባ ትርክት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ትርክት ለዲጂታል ዓለም ተጠቃሚዎች ተደራሽ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል።

"ግድቡ ከውኃ ሙሊት ተሻግሮ ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ እየተንደረደረ በመሆኑ የተያዘው በጀት ዓመት ወሳኝ ጊዜ ነው" ያሉት ደግሞ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው።

በየደረጃው ያሉ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች የሕዝቡን ፍላጎት የሚመጥን የተሳትፎ ሥልት ሊቀይሱ እንደሚገባም አሳስበዋል።

"እኛ ኢትዮጵያውያን ስናብር ምን ማሳካት እንደምንችል፤ ስንለያይ ደግሞ  ምን እንደሚገጥመን ያለፍንባቸው የታሪክ ሂደቶች አሳይተውናል" ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የትብብራችን ውጤት ጥሩ መሳያ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግድቡ ፍጻሜ የዜጎች ርብርብ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥልቶች መጀመራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም