ከቤይሩት 180 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከቤይሩት 180 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) በቤይሩት ችግር ላይ የሚገኙ 180 ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከተፋሰስ አገራት ኤምባሲዎችና የዳያስፖራ አባላት ጋር የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉም ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ስለተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
የዜጋ ዲፕሎማሲ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ያወሱት ቃል አቃባዩ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ ለዜጎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከነዚህም መካከል በሊባኖስ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የጉዞ ሰነድ ያልነበራቸው 180 ዜጎች ሰነድ ስለተዘጋጀላቸው በቅርቡ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ተብሏል።
በየመንም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመቀናጀት ዜጎችን ለመታደግ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሳዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ጋር በመነጋገርም በአገሪቷ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ችግር ላይ የሚገኙትን ዜጎች ድጋፍ ማድረጉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከአባይ ተፋሰስ አገራት ባሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ቆንስላዎችና የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በቀጣናው የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል።
በዲፕሎማሲው መስክ በኢትዮጵያ የተሾሙ የሱዳን፣ የግሪክ፣ የጀርመንና የሞሪታኒያ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ሲያቀርቡ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይም ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስና ዳያስፖራ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ የተመራ ልዑክ በጎረቤት አገር ጅቡቲ ጉብኝት ማደረጉንም ገልጸዋል።
በጉብኝታቸውም ከአገሪቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን፣ እንዲሁም በአገሪቱ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋርም ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ዓመታዊ የዲፕሎማቶች ሰብሰባ እንደሚደረግ ገልጸው፤ በስብሰባው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሥልጠና፣ የኤምባሲዎች አፈጻጸምና የጉብኝት ፕሮግራሞች እንደተካተቱ ገልጸዋል።
በዚህም በየትኛውም የዓለም አገራት ኢትዮጵያን ወክለው የሚገኙ አምባሳደሮች፣ የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና ዲፕሎማቶች ከሰኞ ጀምሮ በተሻሻለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ለ15 ተከታታይ ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ሥልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል።
በዓመታዊ ስብሰባውም የኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም የሚገመገም መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ሥልጠናው "ዲፕሎማሲያዊ ሰላም ለአገር ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወን መሆኑም ተገልጿል።
ከስብሰባው ጎን ለጎን አምባሳደሮቹ በአዳማ፣ ቢሾፍቱና እንጦጦ የተከናወኑ መሠረተ ልማቶችንም እንደሚጎበኙ ገልጸዋል።