በኮሮና ምክንያት የመንግሥት አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ሠራተኞች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኮሮና ምክንያት የመንግሥት አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ሠራተኞች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለዜጎች ወሳኝ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ሠራተኞች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሥራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አሳሰበ።
የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ለ34 የመንግሥት ተቋማት የሚከፋፈል የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ የሙቀት መለኪያና ሠራተኞች ቤታቸው ቁጭ ብለው ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ቴክኖሎጂን አካቶ የያዘ ነው።
የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር ብርሃኑ ፈይሣ በቁሳቁስ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት ቫይረሱ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኞች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሥራቸውን እንዲከውኑ ሲደረግ ቆይቷል።
"ቫይረሱ ከሚያስከትለው የጤና ችግር ባለፈ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ስነ ልቦናዊ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ በተለይ ወሳኝ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ሲደረግ ነበር" ብለዋል።
በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚስተዋለው የቦታ መጨናነቅ የቫይረሱን ሥርጭት ለማስፋፋት ከፍተኛ ሚና አለው።
ይህን ችግር ለመፍታት ሠራተኞችን በግማሽ በመቀነስ ቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደረጉን አስታውሰዋል
ይሁንና ቫይረሱ በኢትዮጵያ በተከሰተበት ጊዜ በተለያዩ ተቋማት ይደረጉ የነበሩ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት የቫይረሱ ሥርጭት በፍጥነት እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት መዘናጋት እየታየ በመሆኑ ሠራተኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ተርሃን ሳሌ በበኩላቸው "በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ በትብብር መከላከል ካልተቻለ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
ቫይረሱ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተቋማቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎችን የሚደግፍ ሲሆን በተለይ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በ34 ተቋማት የአቅም ግንባታ ሥራ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
"ኮሮና ቫይረስ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት እንዳያስተጓጉል በትኩረት መሥራትና ሠራተኞችም ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው ሥራቸውን በማከናወን የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ አለባቸው" ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተወካይዋ አረጋግጠዋል።
ተቋሙ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የፈጠራ ሥራ እንደሚያበረታታና በተለይ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ያላቸውን የፈጠራ ችሎታ ተጠቅመው ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።
ተቋሙ በአገሪቷ በሚከናወኑ የተለያዩ የልማትና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሰራ መሆኑንም ተወካይዋ አመልክተዋል።