ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት እያደረገች ላለው ሥራ ኖርዌ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት እያደረገች ላለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ኖርዌ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በአፍሪካ ሕብረት የኖርዌ መንግስት ተወካይ አስታወቁ።

በሕብረቱ የኖርዌ መንግስት ተወካይ ሚስ ቪግዲሰ አስሉነድ ክሪስቶፎል በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለመደገፍ በጉለሌ እጽዋት ማዕከል ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል።

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ እየሰራች ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የኖርዌ መንግስት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ለምታደርገው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንቅስቃሴ የጀመረውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

"ኖርዌ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት የምትችለውን ድጋፍ ታደርጋለች" ያሉት ተወካይዋ፣ በተለይ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለማጎልበት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አገራቸው በንቃት እየተከታተለች መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

ኖርዌ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያን ስትደግፍ መቆየቷን ያስታወሱት ደግሞ በኢትዮጵያ የኖርዌ ኢምባሲ የፕሮግራም ኦፊሰር ዶክተር ሰለሞን ዘሩ ናቸው።

ዛሬ የተዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሀግብርም አገሪቱ ለምታከናውነው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አጋርነትን ለማሳየት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ሰለሞን እንዳሉት ኖርዌ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የድጋፍ ስምምነት ፈጽማ ወደ ተግባር ገብታለች፡፡

ለዚህም ከአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር በመሆን በአምስት ክልሎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራን የመደገፍ ተግባር መከናወኑን በማሳያነት ገልፀዋል፡፡

"በድጋፉ የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረጉ የደን እንክብካቤ ስራዎች፣ የተጎዱና የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ የሚያደርጉ እንዲሁም የህብረተሰቡን የገቢ ምንጭ የሚያሳድጉ ሥራዎች ተከናውነዋል" ብለዋል፡፡

የኖርዌ መንግስት ከሌሎች የልማት አጋሮቹ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለመደገፍ በተቋቋመ ክላስተር አማካይነት የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኤምባሲው ቅጥር ግቢ እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች በተጨማሪ በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ኤምባሲው ቦታ በመረከብ በየዓመቱ ችግኝ እየተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ባለሙያ አቶ ጎራው በለጠ በበኩላቸው የኖርዌ መንግስት ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስራዋን ለማሳደግ እያደረገች ላለው እንቅስቃሴ የኖርዌ መንግስት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ በተለይ በደን ልማት ዙሪያ ለሚያከናውነው ተግባር እገዛው ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከተተከሉ 4 ቢሊዮን ችግኖች ውስጥ 84 በመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸውን በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን አቶ ጎራው አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም