ቀጥታ፡

ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ዜጎችን አስቀድሞ የማንሳት ሥራ ተሰርቷል---ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15/2012(ኢዜአ) በተያዘው ክረምት ለጎርፍ አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ዜጎችን ቀደም ብሎ የማንሳት ሥራ መከናወኑን ብሔራዊ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። በክረምቱ እስካሁን ድረስ ከ128 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከቄያቸው መፈናቀላቸውም ተመላክቷል።

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ነግዬ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የክረምት የአየር ትንበያ መስጠቱን ተከትሎ ከኮሚሽኑ በተጨማሪ የመንግስት መስሪያ ቤቶችንና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማትን ያካተተ የጎርፍ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ወደስራ ተግብቷል።


በግብረ ኃይሉ ሥር ባሉ ክላስተሮች በተዘጋጀው የመጠባበቂያ ዕቅድ የትኞቹ አካባቢዎች ለጎርፍ ተጋላጭ እንደሆኑንና ምን ያህል ሰዎች ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ተለይተው መቀመጣቸውን አስረድተዋል።

አቶ ነግዬ እንዳሉት በትንበያው መሰረት ትኩረት ለሚሹ አካባቢዎች የጎርፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

መረጃው ለክልል ኃላፊዎችና ለክላስተር ኃላፊዎች እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደርሱ በማድረግ ክልሎች ባላቸው ግብረኃይል ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ነው የገለጹት።


በክልል ደረጃ ያለው ግብረኃይል በአካባቢው ማህበረሰብ ቋንቋ ለህብረተሰቡ መረጃ ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ ስራ መስራቱንም አመልክተዋል።


በዚህም ጥገና የሚያስፈልጋቸው የፍሳሽ ማስወገጃና ቦዮች ካሉ የመስራት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃውን በየጊዜው የማጠናቀር ሥራዎች መሰራታቸውን ነው የጠቆሙት።

በተያዘው ክረምት በጎርፍ አደጋ ከ2 ሚሊዮን ሰዎች ጉዳት ሊደርስባቸው እንዲሁም ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር።

"ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ክረምቱ ከመግባቱ አስቀድሞ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን ከጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች የማንሳት ሥራ ተከናውኗል" ብለዋል።

በዚህም ከደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ቀደም ብሎ ከ10ሺህ በላይ ሰዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፈር ከአደጋ መታደግ መቻሉን ነው የገለጹት። 

"በተደረገው የመረጃ ልውውጥና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ የተጎጂዎችን ቁጥር መቀነስና እስካሁን ባለው ሁኔታ የሰው ሕይወት እንዳያልፍ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል። 

ይህም ሆኖ እስካሁን ከ164 ሺህ በላይ ዜጎች በጎረፍ ሳቢያ የንብረት ውድመት ሲጋጥማቸው 128 ሺህ በላይም ከቄያቸው መፈናቀላቸውን ነው የገለጹት።

"የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ባይከወኑ ኖሮ አደጋው ከዚህም የከፋ ይሆን ነበር ብለዋል" የቡድን መሪው።

በአፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልሎች እስካሁን የጎርፍ አደጋው የተከሰተባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም አቶ ነግዬ ገልፀዋል።

አሁን ላይ ኮሚሽኑ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ቤተሰብ ደረጃ ለአንድ ወር የሚሆን የምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አሁንም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚኖር የሰጠውን ትንበያና ከግድቦች ጋር ተያይዞም ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚገኙ መረጃዎችን ኮሚሽኑ ባለው መዋቅር ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።


ክረምቱ አለመጠናቀቁን ተከተሎ ትኩረት የሚያሻቸውንና ጎርፍ ይከሰትባቸዋል ተብለው የተለዩ አካባቢዎች በመኖራቸው ኀብረተሰቡ የመረጃ ልውውጡን እንዲያጠናክር አቶ ነግዬ አክለው አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም