በሚቀጥሉት 10 አመታት የወጪ ንግድ አመታዊ ገቢን ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት 10 አመታት የወጪ ንግድ አመታዊ ገቢን ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ታቅዷል
አዲስ አበባ ነሐሴ 14/2012 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት 10 አመታት የወጪ ንግድ አመታዊ ገቢን ከሶስት ነጥብ ሶስት ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ለማሳደግ መታቀዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ10 አመት መሪ እቅድ ላይ ውይይት እያደረገ ሲሆን፤ እቅዱ በኢንዱስትሪውና በንግዱ ዘርፍ የነበሩ ክፍተቶችና አስቻይ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።
እቅዱ በኢንዱስትሪውና በንግዱ ዘርፍ ያለውን ትስስር በማጣጣም ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የያዘውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው።
ይህም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከአገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት ያለውን የ6 ነጥብ 8 በመቶ ድርሻ ወደ 17 ነጥብ 8 በመቶ ያሳድገዋል።
በ10 አመታት ውስጥ በዘርፉ የሚፈጠረውን የስራ እድል አምስት ሚሊዮን ማድረስና የአምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በአገር ውስጥ ያላቸውን የገበያ ድርሻ ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ማሳደግም ሌላው የእቅዱ ዋነኛ ግብ ነው።
ከገንዘብ፣ ከግብዓት፣ ከመሰረተ ልማት፣ ከቴክኖሎጂና ከሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ጋር የሚያያዙ ማነቆዎች የንግድና የኢኮኖሚው ዘርፍ የታሰበውን ያህል ውጤት እንዳያመጣ ማድረጋቸውን እቅዱ ይዳስሳል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረጉ ማበረታቻዎች ውጤትን ያማከለ አለመሆን፣ የግብዓት ጥራትና መጠን ማነስ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ የሃይል መቆራረጥና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችም ተነስተዋል።
በንግዱ ዘርፍ ደግሞ የዳበረ የንግድ ትስስር አለመኖር፣ የመረጃ ተደራሽነት ማነስ፣ የቴክኖሎጂ ገበያ ስርአት አለመዘርጋት፣ ለወጪ ንግዱ የሚላኩ ምርቶች በአይነት፣ ጥራትና መጠን አናሳ መሆን፣ ፍትሃዊ የገበያ ውድድር አለመኖሩም ተነስተዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ አስር አመታት እነዚህን ክፍተቶች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተመጋጋቢ እቅድ ማውጣቱን ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።
ከላይ ያሉት ችግሮች ተዳምረው በአገሪቱ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በጣም ውስን እንዲሆኑ አድርጓል።
የወጪ ገበያው ምርቶች ጥቂትና ተመሳሳይ ሆነው እያሉ ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸው ምርቶች መብዛት የወጪና ገቢ ንግዱን ሚዛን እንዲዛባ እንዳደረገውም ተናግረዋል።
በመሆኑም በተለይ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ የማተካካት ስራ ይጠናከራል ብለዋል።
ከዚያ በተጨማሪ ወደ ውጭ የሚላኩ የወጪ ንግድ ምርቶችን በመጠን፣ በአይነትና በጥራት የማስፋት ስራም ይሰራል ብለዋል።
እቅዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የገበያ ውድድርና የኮቪድ 19 ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የራሱ ተፅዕኖ ከሚያደርግባቸው አገራት አንዷ ብትሆንም እስካሁን በወጪ ንግዱ ላይ የጎላ ጉዳት እንዳላደረሰ ተናግረዋል።
ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ የተገኙ አጋጣሚዎችን ሁሉ ለመጠቀም ተሞክሯል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሃምሌ 2012 ዓ.ም ከወጪ ንግዱ 275 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
የአገር ውስጥ ገበያውን አረጋግቶ የወጪ ንግዱንም ለማጠናከር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ተቋቁሞ ምርት ሳይቋረጥ ማምረት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ በኢንዱስትሪዎችና ሌሎች አምራች ዘርፎች ላይ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።