ቀጥታ፡

የሸገርና እንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክቶች ንድፈ ሃሳብ ወደ ተግባር የተቀየረባቸው ማሳያዎች ናቸው... ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 14/2012 (ኢዜአ) የሸገርና እንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክቶች ንድፈ ሃሳብ ወደ ተግባር የተቀየረባቸው ማሳያዎች መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች ገለጹ።

የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ከተጠሪ ተቋማትና በአዲስ አበባ ከሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ዛሬ ፓርኮቹን ጎብኝተዋል።

በሸገርና በእንጦጦ ፓርኮች ''አስደናቂ'' ያሏቸውን የጥበብ፣ የፈጠራ፣ የምህንድስና ስራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የእውቀት፣ የምርምር፣ የፈጠራና የሰው ኃይል ልማት ማዕከል ለሆኑት ተቋማት ፓርኮቹ ንድፈ ሃሳብን ወደ ተግባር ለመቀየር  እንደ ማነቃቂያ ያገለግላሉ ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር እሸቱ ከበደ ፓርኮቹ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመስራት በአጭር ጊዜ የአገርን ምጣኔ ሃብት ማሳደግ እንደሚቻል ማሳያ እንደሆኑ ይናገራሉ።

የተቋማቱ ተማሪዎችና መምህራን መሰል ፕሮጀክቶችን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን ለመድገም እንደሚሰሩም እምነታቸውን ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂክ ማዕከል ምክትል ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ ከፈለች ደምቦባ አዕምሮን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ስኬት ማምጣት እንደሚቻል ከፓርኮቹ የግንባታ ጥበብ ተረድቼያለሁ ሲሉ አስተያየታቸውን  ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው በፓርኮቹ የታየው የምህንድስና፣ የጥበብና የፈጠራ ስራ ለዩኒቨርሲቲው የተግባር ትምህርት እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ እንዲሁም ሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሚሰጥ ትምህርት በቀላሉ ወደ ተግባር ለመቀየር ፓርኮቹ እንደ ናሙና ያገለግላሉ።

ዩኒቨርስቲው በፓርኮች ውሰጥ በሚገኙ እጽዋት ምርምር እንደሚያደርግና ሌሎች ስራዎች እንደሚሰራ በመግለጽ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ "በፓርኮቹ የሃሳብን ትልቅነት ማብላላት የተቻለበት ነው" ሲሉ ምልክታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የተለያየ መልክዓ ምድር በመጠቀም የሸገርና እንጦጦ መሰል ፓርኮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለማልማት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በፓርኮቹ  የሚታዩት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ስራዎች ለኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር እንደሚያገለግሉ አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት ፓርኮች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  በተከታታይ እየተጎበኙ ናቸው።

ፓርኮቹ ባለፈው ሳምንት''የኢትዮጵያ ልክ'' በተሰኘ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለተመልካቾች መቅረባቸው ይታወሳል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም