ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል በታቀደው ህገ-ወጥ ምርጫ ላይ መንግስት ማዕቀብ መጣል አለበት...የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን የሁከትና ብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ በትግራይ ክልል በታቀደው ህገ-ወጥ ምርጫ ላይ መንግስት ማዕቀብ መጣል እንደሚገባው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገለጸ።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በትግራይ ክልል ይደረጋል የተባለው ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሳይሆን ከፌዴራል መንግስቱ ራሳቸውን ላሸሹ ቡድኖች መደበቂያነት እያገለገለ ነው።

በኢትዮጵያ ራሳቸውን አግልለው በአንድ ቦታ የመሸጉ ቡድኖች የሚያካሂዱት ምርጫ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን የጣሰ የሥልጣን ማራዘሚያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም የሚደረገው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማስፈን ይልቅ አገሪቱን የሁከትና ብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የታሰበ ነው ብለዋል።

"በትግራይ ክልል የመሸገው ቡድን ጦርነት እገጥማለሁ እያለ፤ የጦር ነጋሪት እየጎሰመ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሂዳል ማለት ስህተት ነው" ሲሉም ነው ዶክተር አረጋዊ የተናገሩት።

የፌዴራል መንግስቱም ሆነ ኅብረተሰቡ በምርጫ ሰበብ ሊደርስ የሚችለውን አገራዊ ቀውስ ለመከላከል በሰላማዊ መንገድ ምርጫውን ማስቆም አለባቸው ብለዋል።

የፌዴራል መንግስቱ በሰላማዊ ትግል ማዕቀብ መጣልን ጨምሮ ምርጫው እንዳይካሄድና ለምርጫ የሚባክነው ገንዝብ ለልማት እንዲውል ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

ምርጫውን ህዝቡን ከለላ በማድረግ ወንጀላቸውን ለመሸፈን የሚጠቀሙበት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ነው ሲሉ ኮንነውታል።

"ህግ እየጣሱ በምርጫ ሰበብ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረግ በስልጣን መባለግ" ሲሉም ነው የገለጹት።

የትግራይ ወጣቶችም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ጦርነት ሳይሆን ሰላምና በጋራ መልማት ቢሆንም ቀደም ሲል የነበረው አገዛዝ ሌብነትን እያበረታታ በአገሪቱ ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ አድርጓል ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት የተገነባው መንግስታዊ ድጋፍ ያለው ሌብነት በትግራይ ክልል ብቻ መስራት የሚችሉ ከ30 በመቶ በላይ ወጣቶችን ሥራ አጥ አድርጓቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም