የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብና የመጠጥ አቅርቦቱን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብና የመጠጥ አቅርቦቱን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 14/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የምግብና የመጠጥ አቅርቦቱን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ኢትዮጵያዊ ጣዕምና ተወዳጅነት ያላቸውን ምግብና መጠጥ ለመንገደኞቹ ለማቅረብ ትኩረትም ይሰጣል ብሏል ።
አየር መንገዱ ዛሬ ከኢትዮጵያ የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች ማሕበር ጋር የሚሰራበትን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የሰው ኃይል አስተዳደር ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ዋሲሁን አስረስና የማሕበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሔኖክ ዘሪሁን ፈርመዋል።
አቶ ዋሲሁን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አየር መንገዱ ከሌሎች አቻ አየር መንገዶች ጋር ከሚወዳደርባቸው መስኮች አንዱ የምግብና የመጠጥ አቅርቦት ይገኝበታል።
በመሆኑም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያዊ ጣዕምና ተወዳጅነት ያላቸውን ምግብና መጠጥ ለመንገደኞቹ ለማቅረብ ከማሕበሩ ጋር በቅንጅት ይሰራል።
ስምምነቱ የአየር መንገዱ የምግብ ዝግጅትና የሰራተኛ መመገቢያ ክፍሎችን ለማዘመንና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው አመልክተዋል።
በተጨማሪም አየር መንገዱ ያሉት የምግብ ባለሙያዎችን ጨምሮ የሚያስተዳድረው የስካይላይት ሆቴልን የምግብ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያዊ ምግብን ለተቀረው ዓለም በስፋት ለማስተዋወቅ፣ ለምግብ ዝግጅት ክፍል ባለሙያዎች ተከታታይ ስልጠናዎችና ሙያዊ እገዛ ለመስጠት ይረዳዋል ብለዋል።
አቶ ሔኖክ በበኩላቸው ማሕበሩ ለአየር መንገዱ ባለሙያዎች በተከታታይ ስልጠና በመታገዝ የኢትዮጵያ ብሔር/ ብሔረሰቦችን ምግብና ጣዕም ለዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ለማቅረብ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በተጨማሪም አየር መንገዱ የምግብ አገልግሎት ሳይንሳዊነቱን ጠብቆ እንዲሰጥ ፣ኢትዮጵያዊ ባሕልን ለማስተዋወቅና የምግብ ቱሪዝምን ለማሳደግ ተቀናጅቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።