በደቡብ ወሎ ዞን በተካሄደ የኮሮና መከላከል ዘመቻ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ተመረመሩ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን በተካሄደ የኮሮና መከላከል ዘመቻ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ተመረመሩ
ደሴ ነሐሴ 14/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን የኮሮና ቫይርረስን ለመከላከል እንዲያግዝ በተካሄደው ዘመቻ ከ6 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ላይ ናሙና ተወስዶ መመርመር መቻሉን የዞኑ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ ፀሐፊና የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ይስማው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከነሐሴ 1/2012 ጀምሮ የግንዛቤ ፈጠራና የምርመራ ዘመቻ እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
በዘመቻው ሥራው ሁለት ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎችን በማሠማራት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና በቫይረሱ መያዛቸው የሚገመቱ ሰዎችን ምርመራ በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዚህም 6ሺህ 921 ናሙናዎችን ለመመርመር ታቅዶ እስከትናንት ድረስ 6ሺህ 535 ሰዎችን መመርመር መቻሉን አስረድተዋል።
ከተመረመሩት ውስጥም 83 ግለሰቦች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ቤት ለቤት በተካሄደው አሰሳም 600 ሺህ የሚጠጉ ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ ተጋላጭ የሆኑ 622 ሰዎች መለየታቸውን አመልክተዋል።
"በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ በቀን 461 ናሙና እንድንመረምር እቅድ ቢሰጠንም የቫይረሱ ስርጭት በመስፋፋቱ በቀን እስከ አንድ ሺህ ድረስ እየመረመርን እንገኛለን" ብለዋል።
ይህም የበሽታው መስፋፋት የሚያመለክት በመሆኑ ለህክምና ከተመረጠው የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል በተጨማሪ በወረዳዎች የህክምና ማዕከል ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።
በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋትና ቸልተኝነት ለማስተካከል በየደረጃው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በአጠቃላይ እስካሁን ከ10 ሺህ 800 በላይ ናሙና ተወስዶ 121 ግለሰቦች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውም ተመልክቷል፡፡