"በህዳሴ ግድብ በተገኘው ድል ሳንኩራራ በቀጣይ ግድቡን መጨረስ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ - ኢዜአ አማርኛ
"በህዳሴ ግድብ በተገኘው ድል ሳንኩራራ በቀጣይ ግድቡን መጨረስ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 14/2012 (ኢዜአ) "በህዳሴ ግድብ በተገኘው ድል ሳንኩራራ በቀጣይ ግድቡን መጨረስ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል" ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የግድቡ ግንባታ አሁናዊ ሁኔታዎች ላይና በቀጣይ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ የግድቡ የግንባታ ሥራ የደረሰበትን ደረጃና በቀጣይ በሚሰሩ ተግባራት ላይ ገለፃ አድርገዋል።
ኢንጅነር ክፍሌ በገለፃቸው ፕሮጀክቱ አሁን ላይ የሲቪል ስራ አፈፃፀሙ 88 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱንና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው 46 ነጥብ 5 በመቶ ያህል መጠናቀቁን አብራርተዋል።
የሀይድሮ ስቲል ስትራክቸር ሥራ 33 በመቶ መድረሱን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የኮርቻ ግድብ ሥራ 99 በመቶ ተገባዷል ብለዋል።
ለዘጠኝ ዩኒቶች የሚሆን ተርባይን ቦታው ላይ መድረሱንም ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል።
የግደቡን የ568 ሜትር ከፍታ በቀጣይ ዓመት ወደ 595 ሜትር ለማድረስ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ በዚህ ዓመት በተከናወኑ ተግባራት በታቀደለት ጊዜ መከናወናቸውን አመልክተዋል። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸምም 75 በመቶ መድረሱንም ኢንጅነር ክፍሌ አስምረውበታል።
ግድቡ በታቀደለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ምን አልባትም ተግዳሮት ሊሆን ይችላል ያሉትን የቢሮክራሲ የፋይናንስ ችግርና የኮሮና ወረርሽኝ ጉዳዮችንም ትኩረት እንዲደረግባቸው አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ''በዚህ ዓመት በግድቡ ላይ በተሰራው ጠንካራ ስራና በተገኘው ድል ሳንኩራራ ለተሟላ ድል ለፍፃሜው በትጋት መስራት ይገባል'' ብለዋል።
እስካሁን የተከናወኑት ሥራዎች ''እጅግ የሚያኮራ'' በማለት የገለጹት ዶክተር ዓቢይ፣ ''ያቀድነውን መፈጸም እንደምንችል ለእኛም ለወዳጆቻችን ጨምሮ ለሚጠራጠሩንም ያሳየንበት ድል ነው'' ሲሉም ክንውኑን ገልጸውታል።
የመንግስታትና የግለሰቦች መቀያየር ቢኖርም፤ በአገራዊና ብሄራዊ ፍላጎት ላይ ድርድር እንደሌለም አስረድተዋል።
በመሆኑ ዓመቱን ''በኢትዮጵያውያን ወኔ እሳቤ ያጠናቀቅነው የድል ዓመት ነው'' ብለዋል።
ግድቡ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን፤ የነፃነት አርማ በመሆኑ በአፍሪካ ነፃ የሆነች አገር ብቻ ሳይሆን፤ ነፃ ሆና የምትቀጥል አገር መሆኗን እንዳሳየችበት ተናግረዋል።
ግድቡን ለውጤት ማብቃት የኢትዮጵያውያንን ስነ ልቡና ከፍ ማድረግ በመሆኑ ግድቡን በታቀደለት ጊዜ አጠናቆ ወደ ሌሎች አዳዲስ ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ማምራት እንደሚገባ አስምረውበታል።
ይህንን ለማድረግ እሰከ ህይወት መስዋትነት ድረስ መከፈል ያለበት መስዋትነት ተከፍሎ እያንዳንዱ አመራር ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የተሟላ ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሳስበዋል።
ከዚህ አንፃር የግድቡ ግንባታ እንዳይስተጓጎል ከጅቡቲ ወደብ አንስቶ በትራንስፖርት እንዲሁም በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያለው ሁኔታ ምቹ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።
በግድቡ ግንባታ እንቅፋት የሚሆን የትኛውም ቡድን ሆነ ግለሰብ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የተጋረጠ አደጋ በመሆኑ ሁሉም ሊመክተው ይገባዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ።
ከዚህ አንፃር የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የሚደረግ እንቅስቃሴን በመከላከል በቀጣዩ ዓመት 18 ነጥብ 4 ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ለመሙላት መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።