ቀጥታ፡

ተቋማቱ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 14/2012 (ኢዜአ) ሦስት ተቋማት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁስ ለጤና ሚኒስቴር ለገሱ።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በቅርቡ ማምረት የጀመረውን 100 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ድጋፍ አድርጓል።

ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል 100 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) እንዲሁም 400 ሊትር ሳኒታይዘር ለግሷል።

አስትራ ዜንካ የተሰኘው ተቋም ደግሞ 35 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) እንዲሁም 6 ሺህ መመርመሪያ ኪቶች ድጋፍ አድርጓል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ተቋማቱ ከሚኒስቴሩ ጋር በመስራት ውጤታማ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ወረርሽኙን ለመከላከል ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል።

በድጋፍ የተሰጡት የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁስ ወረርሽኙን ለመከላከል በግንባር ቀደምነት ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች  አገልግሎት እንደሚውሉ ገልጸዋል።

ድጋፉ በተለይም ወረርሽኙ እየተስፋፋ ባለበት ወቅት መለገሳቸው የአቅርቦት ችግርን ያቃልላሉ ብለዋል።

ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩና ድጋፍ ማድረግ ያልጀመሩ ተቋማትም ልገሳ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኮሮና ቫይረስን መከላከል የሚቻለው በጋራ ጥረት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ድጋፍ ያደረጉት ተቋማት አጋርነታቸውን እንዲያጠናከሩ አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡም  ወረርሽኙ እየተስፋፋ መሆኑን በመገንዘብ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲተገብር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም