ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የኮቪድ-19 ግንዛቤ የመፍጠር ፕሮጀክት በመጪው መስከረም ወደ ስራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የኮቪድ-19 ግንዛቤ የመፍጠር ፕሮጀክት በመጪው መስከረም ወደ ስራ ይገባል
አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2012(ኢዜአ) ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የኮቪድ-19 የግንዛቤ መፍጠርና መቆጣጠር ላይ የሚሰሩበት ፕሮጀክት በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ወደ ስራ እንደሚገባ ተገለጸ።
ፕሮጀክቱ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን 21 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ብሌን አስራት የፕሮጀክቱ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተገባደዱ መሆናቸው በመስከረም ወር ወደ ስራ እንደሚገባ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ አላማ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በመላ የአገሪቱ ክፍሎች የግንዛቤ መፍጠርና የህክምና አገልግሎቱ እንዲሁም የሚደረጉ ድጋፎች ሁሉን አሳታፊ መሆናቸው ቁጥጥር ማድረግ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የግንዛቤ መፍጠርና የቁጥጥር ስራው በ17 የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገው ገንዘብ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መርሃ ግብር ምዕራፍ ሁለት ድጋፍ ከሚያደርጉ ለጋሾች የሚገኝ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የስምምነት ፊርማ እንደሚፈረም ጠቁመዋል።
መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ያሉ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አቅም በመገንባት የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት በማስፈን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም (ዴኤፍአይዲ)፣ የኖርዌይ፣ ስዊድንና አየርላንድ መንግስት ድጋፍ እንደሚያድርጉ ወይዘሮ ብሌን አስረድተዋል።
የአገልግሎት ተደራሽነት መኖሩን ማረጋገጥና የግንዛቤ ለውጥ ማምጣት ከፕሮጀክቱ የሚጠበቁ ግቦች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭቱን ለመከላከል ዘላቂነት ያላቸው ስራዎች መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ከፕሮጀክቱም መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ በዘላቂነት በጉዳዩ ላይ እንደሚሰራ አመልክተዋል።