ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የተገነቡ ግድቦች የጎርፍ ጉዳትን ለመቀነስ ማገዙን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ

ድሬዳዋ ነሐሴ 14 / 2012(ኢዜአ) በድሬዳዋ ቀደም ሲል የተገነቡ ግድቦች የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በሚመጣው ጎርፍ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ማገዙን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ። 

የአስተዳደሩ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው በ1998 ዓ.ም የደረሰውን የከፋ የጎርፍ ክስተት ተከትሎ በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመከላከያ ግድቦች ተገንብተዋል።

ግድቦቹ ከምስራቅ ሐረርጌ በሁለት አቅጣጫዎች ወደ ከተማው የሚፈስን ጎርፍ በመከላከል በሰውና ንብረት ላይ ያደርስ የነበረውን ጉዳት  ለመቀነስ ማገዙን ተናግረዋል።

በተራቆቱ ተፋሰሶች የተከናወኑ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎችም አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል ።

የተገኙ መልካም ተሞክሮቹን አስፍቶ በማጠናከር የጎርፍ ጉዳት ተጋላጭ በሆኑ ገጠር ቀበሌዎች በ10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል ።

የድሬዳዋ ከተማ  አስተዳደር  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልጀዋዱ መሐመድ በበኩላቸው አስተዳደሩ 10 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ከዚህ ቀደም ለተገነቡ የጎርፍ መከላከያዎች አስፈላጊውን ጥገና ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል ።

ጥገና የሚደረግላቸው ግድቦች፣ ተፋሰስ መውረጃዎችና ድልደዮችን የመለየትና የቁሳቁስ ግዥ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የከተማውን የጎርፍ ተጋላጭነት ስጋት በዘላቂነት ለመፍታት ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሃብት የማፈላለግ ስራ እየተካሄደ  ነው።

በድሬደዋ ሰሞኑን  ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ ጎርፍ ቢከሰትም በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌላ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የለውጥ ስራዎች እና የህዝብ ግንኘነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ ገልጸዋል።

ሆኖም በከተማው ቀፊራ ገበያ አትክልት ላይ መጠነኛ ፣ አፍካት እና ሐምዳኢል በተባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የጎርፍ መከላከያ ግድብና መሸጋገሪያ ድልድይ  ጉዳት እንደደረሰባቸው   አመልክተዋል።

ሐምሌ 29 ቀን 1998 ዓ.ም. ሌሊት በድሬዳዋ  ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተወስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም