በጎንደር ከተማ ህግ የተላለፉ ከ680 በላይ አሽከርካሪዎችና የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ህግ የተላለፉ ከ680 በላይ አሽከርካሪዎችና የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ጎንደር ነሐሴ 14/2012( ኢዜአ) በጎንደር ከተማ መንግስት ኮሮናን ለመከላከል ያወጣውን አዋጅ የተላለፉ ከ680 በላይ አሽከርካሪዎችና የንግድ ድርጅቶች እርምጃ እንደተወሰደባቸው ፖሊስ ገለጸ።
የኮሮና መከላከል ግብር ኃይል አባል የሆነው የከተማው ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት እርምጃው የተወሰደው በሐምሌ እና ነሐሴ 2012 ዓ.ም ወራት ውስጥ ነው።
በዚህም አዋጁን ጥሰው እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 28 አሽከርካሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ባለማድረግ እያንዳንዳቸው በአንድ ሺህ ብር መቀጣታቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም 75 የንግድ ድርጅቶች ብዛት ያላቸው ሰዎችን ለቫይረሱ በሚያጋልጥ ሁኔታ አሰባስበው ጫት ሲያስቅሙና ሺሻ ሲያስጨሱ በመገኘታቸው ማህበራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው በተመሰረተባቸው ክስ እስከ 8 ወራት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሌሎች 548 ግሰቦችና ድርጅቶችም ትርፍ ሰው በመጫን፣ በህገ ወጥ መንገድ መጠጥ በመሸጥና ካራንቡላ በማጫወት በፈጸሙት ጥፋት ክስ ተመስርቶባቸው በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን 900 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲከፍሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ሌሎች 32 ግለሰቦችና ድርጅቶች ደግሞ ጥፋታቸውን አርመውና ተጸጽተው በመገኘታቸው በምክር እንዲታለፉ መደረጋቸውን የጠቆሙት ኢንስፔክተሯ ሌሎች በተጨማሪም 120 ግለሰቦችም ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢንስፔክተሯ ገለጻ የከተማው ፖሊስ ከግብረ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት በገበያ እና ህዝብ በሚሰባሰብባቸው ስፍራዎች ህብረተሰቡ ርቀቱን እንዲጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲጠቀም ቅስቀሳና ትምህርት እየሰጠ ነው፡፡
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ደሴ ኃይሉ በሰጡት አስተያየት የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን እየተነገረ ቢሆንም ህብረተሰቡ እራሱን ከበሽታው ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥንቃቄ እምብዛም እንደሆነ በአካባቢያቸው መታዘባቸውን ተናግረዋል።፡
አዋጁን ለማስፈጸም በየደረጃው ኃላፊነት የተሰጠው አካል እርምጃዎችን በመውሰድ ህብረተሰቡ የሚያሳየውን መዘናጋትና ቸልተኝነት ማስተካካል ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ሹምዬ አካሉ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡