የመጨረሻ ሳምንት ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ይጠበቃሉ

73
አዲስ አበባ 5/2010 አሸናፊና የሚወርዱ ክለቦች የሚለይበት የመጨረሻ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከአርብ ጀምሮ ይካሄዳሉ፡፤ በፕሪሚየር ሊጉ  ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ 52 ነጥብና 19 ጎሎች 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ይዘው ዋንጫውን ለማንሳት ተፋጥጠዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን በታሪኩ ለ15ኛ ጊዜ ለማንሳት የሚጫወት ሲሆን ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለውና ጥሩ ፉክክር እያሳየ ያለው ጅማ አባ ጅፋር ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት የመጨረሻ ጨዋታውን ያደርጋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ጅማ ላይ ጅማ አባጅፋር ከአዳማ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ እሁድ ስምንት ሰዓት ላይ  የሚደረግ ይሆናል። የመውረድ ስጋት ያለባቸው አርባ ምንጭ ከተማ፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ፣ ወላይታ ድቻና ድሬዳዋ ከተማ  ጨዋታቸውን ቅዳሜ የሚያደርጉ ይሆናል። በመርሀ ግብሩ መሰረት ሰበታ ላይ ወልዲያ ከተማ ከወላይታ ድቻ፣ ወልዋሎ ከድሬዳዋ ከተማ ዓዲግራት ላይ፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከሲዳማ ቡና ሰበታ ላይ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ከፋሲል በአርባምንጭ ስታዲየም ቅዳሜ በተመሳሳይ ዘጠኝ ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል ። አርብ መከላከያ ከደደቢት በአራት ሰዓት እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከመቀሌ ከተማ ስምንት ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ ሌላው በመጨረሻው ሳምንት የሚካሄድ  ጨዋታ ነው። ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባ ጅፋር በእኩል 52 ነጥብና 19 ጎሎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ መቀሌ ከተማ በ49 ነጥብ፣ ኢትዮጵያ ቡና በ47 ነጥብ፣ አዳማ ከተማ በ44 ነጥብ እንዲሁም ፋሲል ከተማ በ41 ነጥብ ከ3ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ወላይታ ድቻና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በእኩል 32 ነጥብ እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማ በ30 ነጥብ ከ12 እስከ 16 ያለውን ደረጃ ይዘው በሊጉ ግርጌ ስር በመቀመጥ ወራጅ ቀጠናው ላይ ይገኛሉ። ወልድያ ከተማ አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም