ቀጥታ፡

ለህዳሴ ግድብ ቦንድ የገዙ ዜጎች የመመለሻ ጊዜው ቢደርስም ዳግም በመግዛት ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 14/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀደም ሲል ቦንድ ለገዙ ዜጎች የመመለሻ ጊዜው ቢደርስም ቦንዱን በማደስ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ከጅማሮው እስካሁን ለግድቡ ስኬት የቻሉትን ሁሉ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በርካቶች ቦንድ በመግዛት ድጋፍና አጋርነታቸውን በማሳየታቸው ግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ላይ የደረሰ ሲሆን ለፍፃሜ ለማብቃትም ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በመሆኑም ቀደም ሲል ቦንድ ገዝተው የነበሩ ዜጎች የቦንዱ መመለሻ ጊዜ ቢደርስም ወለዱን ጨምሮ ዳግም ቦንድ እየገዙ ድጋፋቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ተገልጿል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም እንደገለጹት፤ የድጋፍ ማሰባሰቡ ሂደት እንደቀጠለ ነው።

ከዚህ ቀደም ቦንድ የገዙ ሰዎች ዳግም ቦንድ ሲገዙና ሲያድሱ ለግድቡ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፈጠራቸው መልካም አጋጣሚዎችና ሁነቶች መካከል አንዱ የቁጠባ ባህልን ማሳደግ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሃይሉ ፤ የቦንድ ግዥው የአገርን የኢኮኖሚ እድገት በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም