ባለሀብቱ 5 ሺህ የአፍና አፍንጫ ጭምብል ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ባለሀብቱ 5 ሺህ የአፍና አፍንጫ ጭምብል ድጋፍ አደረጉ
ደሴ ፣ ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ አንድ ባለሀብት አምስት ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ድጋፍ አደረጉ።
የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ደምስ እንድሪስ እንደገለጹት ባለሀብቱ የሰጡት ድጋፍ ለዞኑ የፀጥታ ኃይል አባላት የሚውል ነው።
ባለሀብቱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አቶ ደምስ አመስግነው ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዞኑ ሰላምና ደህንነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል ጌታሆይ ዘገዬ በበኩላቸው ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ የፀጥታ ኃይሉ ራሱን ለችግር አጋልጦ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ ነው ብለዋል።
አባላቱ ሕግና ደንብ ለማስከበር በሚያደርጉት ጥረትም ለቫይረሱ ተጋላጭ በመሆናቸው ድጋፉ ራሳቸውን ከበሽታው እንዲከላከሉ የሚያግዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ድጋፉን ያደረጉት ባለሀብት አቶ ሰይድ አህመድ ራሱን ለቫይረሱ አጋልጦ ሕዝብን እያገለገለ ላለው የፀጥታ ኃይል እንዲውል አስበው መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ተመሣሣይ ድጋፍ በማድረግ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።