የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ በኮቪድ-19 ለችግር ለተጋለጡ አካል ጉዳተኞች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ በኮቪድ-19 ለችግር ለተጋለጡ አካል ጉዳተኞች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ አካል ጉዳተኞች ከ164 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። መድረኩ እስካሁን ለኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች በአይነትና በገንዘብ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ ያደረገውን ድጋፍ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን አስረክቧል።
ድጋፉ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለችግር ለተጋለጡ 95 አካል ጉዳተኞች የተበረከተ ነው።
አጠቃላይ ለቁሳቁስ ድጋፉ ከ164 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ብሌን አስራት ኮቪድ-19 ከተከሰተ ጀምሮ መድረኩ ኮሚቴ አቋቁሞ በስሩ ካሉ ድርጅቶች ድጋፍ ሲያሰባስብ መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው ብሔራዊ የሀብት አሰባሰቢ ኮሚቴ ገቢ ማድረጉን አመልክተዋል።
ከተሰበሰበው ቀሪ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንና የዛሬው ድጋፍ የዚሁ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው የአሁኑ ድጋፍ ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ ለስምንተኛ ጊዜ የተደረገ ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁንም ከተለያዩ አካላት በማሰባሰብ ከ17 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ፌዴሬሽኑ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ 800 አካል ጉዳተኞች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቶማስ ኩዊ መንግስት፣ ሲቪክ ማህበረሰቡና ህብረተሰቡ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች በበኩላቸው ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፉ ዘላቂነት ባለው መልኩ በቫይረሱ ኢኮኖሚያዊ ጫና የደረሰባቸውን አካል ጉዳተኞች ማካተት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ከድጋፉ በኋላ በስነ-ስርዓቱ የተገኙ አካላት በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ቅጥር ግቢ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።