ቀጥታ፡

በሁመራ ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 18 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኘ

ሰቲት ሁመራ፣ ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) በሁመራ በኩል ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ18 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ገለጸ።

በኮሚሽኑ የሁመራ ቅርንጫፍ የውስጥ ዕቃዎች አወጣጥ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሓድጊአምበስ ገብረሥላሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት ገቢው የተገኘው በግንቦትና ሰኔ 2012 ዓ.ም ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ  ምርቶች ነው።

ወደ ውጭ  የተላኩት የግብርና ምርቶች 50ሺህ ኩንታል ሰሊጥና በቁጥር 850 ግመሎች መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም የተገኘው ገቢ ከ18 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርቶቹ ከተላኩባቸው ሀገራት መካከል ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ቻይናና  እሥራኤል እንደሚገኙበት  አስተባባሪው አስታውቀዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ተቀዛቅዞ የቆየውን የቁም እንስሳት ንግድ መነቃቃት ማሳየቱን የገለጹት ደግሞ በቁም እንስሳት ንግድ የተሰማሩት አቶ ፀዳል ተክሉ ናቸው።

በሁመራ በኩል ከ500 በላይ ግመሎች ወደ ውጭ መላከቸውን ጠቅሰው ተቀዛቅዞ የቆየውን የቁም እንስሳት ንግድ አሁን ተስፋ ሰጪ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌላው በቁም እንስሳት ንግድ የተሰማሩት አቶ ፀጋዬ ገብረክርስቶስ በበኩላቸው 200 ግመሎች ወደ ሱዳን  መላካቸውን ተናግረዋል።

በሁመራ የእንስሳት ጤንነት መመርመሪያ ማዕከል /ኳራንታይን/ አገልግሎት መጀመሩ የንግድ አሰራሩ ግልጽና አስተማማኝ እንዲሆን ረድቶናል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግንቦት በፊት በነበሩት አሥር ወራት በሁመራ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ90 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም