ቀጥታ፡

ለሕዳሴው ግድብ ድጋፉን እንደሚያጠናክር የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሓሴ 13/2012(ኢዜአ) የሕዳሴው ግድብ የግንባታ ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።

ፌደሬሽኑ ዘንድሮ ከ40 ሺህ ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሥራ ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታት ያለፈ ሲሆን በራስ አቅም እየተገነባ ላለው ለዚህ ግድብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ አካል ጉዳተኞች የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለዚህም የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሥራ በተጀመረ በሳምንቱ የፌዴሬሽኑ አባላት 10 ሺህ ብር ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውንም አስታውሰዋል።

ዘንድሮ ፌደሬሽኑ ከ40 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት አቶ አባይነህ፣ አባላቱ ግንባታው ያለበትን ሂደት በአካል ተገኝተው መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

ፌደሬሽኑ በቀጣይም ለሕዳሴው ግድብ የጀመረውን ድጋፍ በማጠናከር ሁሌም ከመንግስት ጎን ይቆማል።

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ በአካል ጉዳተኞችና በተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ደስታ መፍጠሩንም ነው ያመለከቱት።

ፌዴሬሽኑ ከሱዳንና ከግብጽ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ጋር ባለው የሥራ ግንኙነት የሕዳሴ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ለማስረዳት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ፌደሬሽኑ ከ100 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አቶ አባይነህ ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከአገር ውስጥና ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ከ13 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡ ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተጠናቀቀው የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመትም ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ745 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም