የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመጠበቅ በቅንጅት መሥራት ይገባል - ባለሥልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመጠበቅ በቅንጅት መሥራት ይገባል - ባለሥልጣኑ
ባሕርዳር፣ ነሐሴ13/2012(ኢዜአ) የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በመጠበቅና በማልማት ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ።
ባለሥልጣኑ በፓርኩ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከአማራ ክልል የተለያዩ ተቋማት ጋር የጋራ ሥምምነት ለመድረስ ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥር ለብሔራዊ ፓርኮች አደጋ እየሆነ ነው።
በአማራ ክልል በፌደራል መንግሥት ከሚተዳደሩት ሁለት ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መሆኑን አመልክተዋል።
ሕገወጥ ሠፈራ፣ እርሻና የዱር እንስሳት አደን፣ ልቅ ግጦሽ፣ ሰደድ እሳትና የወሰን ጉዳዮች ፓርኩን ከአደጋ መዝገብ ዝርዝር ውስጥ አስገብተውት እንደነበር አስታውሰዋል።
በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ሌሎች ብርቅዬ እንስሳትና አእዋፍ እንዲሁም የዕፅዋት ዝርያዎች እንዲመናመኑም ምክንያት ሆነው እንደነበርም አውስተዋል።
የፌደራል፣ የክልልና የአካባቢው አስተዳደሮች ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ፓርኩን ከአደጋ መዝገብ ዝርዝር ማሰረዝ ተችሏል ብለዋል።
በፓርኩ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት አስተማማኝ ዋሰትና እንዲኖረው ለቀሪ ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጥ አቶ ኩመራ ጠቁመዋል።
ፓርኩ ተመልሶ ወደ አደጋ መዝገብ እንዳይገባ ለማድረግ ባለሥልጣኑ ከክልሉ የተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የሥምምነት ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
"የሰነድ ስምምነቱ ዋና ዓላማም ፓርኩን በመጠበቅና በማልማት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው" ብለዋል።
ፓርኩን ለማልማትና ለመጠበቅ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ለፓርኮችና ጥብቅ ሥፍራዎች ልማት ተኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተጋረጠን አደጋ በጥናት በመለየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለሥልጣኑ ጋር በመተባበር ያላሰለሰ ጥረት መድረጉንም ጠቅሰዋል።
በፓርኩ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሕገወጥ ሠፋሪዎችን ወደ ደባርቅ ከተማ በማምጣት ቦታ፣ የቤት መሥሪያና መተዳደሪያ ገንዘብ በመስጠት የማስፈር ሥራ መሰራቱን አስታውሰዋል።
"የፓርኩን ስፋት ከ236 ሜትር ስኩዬር ወደ 412 ሜትር ስኩዬር በማሳደግ በውስጡ የሚገኙ ብርቅየ እንስሳት ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል" ብለዋል ።
"ፓርኩ ለጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምና ምፅዋ አማካይ መሆኑ በአገራችን ከሚጎበኙ ፓርኮች ግንባር ቀደም አድርጎታል" ያሉት ደግሞ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ለምለሙ ናቸው።
ፓርኩ ለፊልም ሥራ፣ ለጥናትና ምርምርና ለሌሎች ተያያዥ ሥራዎች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
ፓርኩ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር የመሠረተ ልማት፣ የአስተዳደርና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ችግር በመፍታት መጠበቅና ማልማት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ለውይይት የቀረበው የጋራ ሥምምነት ሰነድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ በመሆኑ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት ፓርኩን በዘላቂነት በመጠበቅ ለዘላቂ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማዋል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን አዳነ የፓርኩን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ፓርኩና ማኅበረሰቡ ተጣጥመው የሚዘልቁበትን ሥልት ቀይሶ መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሥምምነቱ የተካተቱ ተቋማት በተናጠልና በቅንጅት በመሥራት የፓርኩን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ይሰራል ብለዋል።
በባሕርዳር ከተማ ትናንት በተካሄደው የውይይት መድረክ በቀረበው የጋራ ሥምምነት ሰነድ ዘጠኝ የክልልና የፌዴራል ተቋማት በቅርቡ ተፈራርመው ወደ ሥራ እንደሚገቡተገልጿል።