የገቢዎች ሚኒስቴር በዘንድሮው በጀት ዓመት 290 ቢሊየን ብር ገቢ ለማሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የገቢዎች ሚኒስቴር በዘንድሮው በጀት ዓመት 290 ቢሊየን ብር ገቢ ለማሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13/2012 (ኢዜአ) የገቢዎች ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት 290 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከፊታችን መስከረም ጀምሮ የጉምሩክ ሥራዎችን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግም ዝግጅቱን አጠናቋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው የተቋሙን ያለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም እንዲሁም በ2013 በጀት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት 270 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 233 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 86 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካቱን ገልጸዋል።
ገቢው ከባለፈው የ2011 የግብር ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ17 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ አለው።
ከገቢው ውስጥም ከአገር ውስጥ ገቢ 128 ቢሊዮን በመያዝ 84 በመቶ ሲሸፍን፣ የጉምሩክ ገቢ 104 ነጥብ 9 ቢሊዮን፣ እንዲሁም ሎተሪ 152 ሚሊየን ገቢ ተገኝቷል።
አመራርና ሠራተኛው ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ተግባብቶ በመሥራት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ ታሪፍ ማሻሻያ፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር፣ ለግብር ከፋዮች ዕውቅና መስጠት፣ የዋጋ ትመና አሰራር ማሻሻያ የማድረግ ሥራ መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የገቢ አሰባሰብ አቅም እያደገ ቢመጣም አሁንም ኢትዮጵያ በሁሉም የግብር ዓይነቶች የምታመነጨው ገቢ ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት አማካይ አገራዊ ምርት ጥምርታ ያነሰ እንደሆነ ገልጸዋል።
በባለፈው በጀት ዓመት የውጭ ንግድን ለማሳለጥ የኮንቴነሮች የደረቅ ወደብ ቆይታ በመቀነስ፣ አገልግሎቱንም በቴክኖሎጂ በመታገዝ የአገልግሎት አሰጣጥ የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የግብር ከፋዩን የሕግ ተገዥነት ለማሳደግ የታክስ ኦዲት ምርመራ ሥራዎች መከናወናቸውን፣ በክንዋኔውም ኦዲት ከተደረጉት መካከል 1 ሺህ 522 የኦዲት ግኝት ከአምስት ቢሊዮን ብር መወሰን መቻሉን ተናግረዋል።
በጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማጭበርበርን በመከላከል በአጠቃላይ 27 ቢሊዮን ብር መንግሥት ሊያጣ የነበረውን ሀብት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በታክስ ማጭበርበር በተደረገ የክትትል ሥራም 274 ድርጅቶች ያለደረሰኝ ግብይት መፈጸማቸውን፣ 223 ሀሰተኛ ማንነት ያላቸው ድርጅቶች መለየታቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ቁጥጥር 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አፈጻጸም እንዳለው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 49 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ጠቅሰዋል።
በነዚህ የታክስ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ ወንጀሎች ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ማኅበረሰቡም ልማት የሚመጣው ከሚሰበሰበው ገቢ መሆኑን ተገንዝቦ መክፈል የሚገባውን ግብር እንዲከፍል ጠይቀዋል።
ከዚህም በኋላ ሀሰተኛ ደረሰኝን ለመከላከል በኦዲት ምርመራው የሚከናወነው የግብይት ደረሰኞች እውነተኛ ስለመሆናቸው ከተረጋገጠ ብቻ አንደሚሆን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ባደረገው የታክስ ዕዳ ስረዛም እስከ 2007 ዓ.ም የግብር ዘመን ድረስ በፍሬ ግብርና በመቀጫ ከ2 ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ግብር ከፋዮች በድምሩ 34 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰረዙን ገልጸዋል።
ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም የግብር ዘመንም ግብር ከፋዮች የወለድና መቀጫ ምህረት በማድረግ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መሰረዝ ሲቻል ከዋናው ፍሬ ግብር ደግሞ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እንደተሰበሰበ ገልጸዋል።
በ2013 በጀት ዓመት ደግሞ 290 ቢሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በዚሀም ከአገር ውስጥ ገቢ 164 ቢሊዮን፣ ከጉምሩክ 125 ቢሊዮንና ከሎተሪ 168 ሚሊየን ብር ድርሻ እንዳላቸው አብራርተዋል።
መንግሥት ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የወሰደው እርምጃ፣ የኮቪድ 19 ተጽዕኖ፣ የተቋማዊ አሰራርና አደረጃጀት፣ የኢንተርኔት ታክስ ሥርዓት፣ የዋጋ ታሪፍ ማሻሻያና ዲጂታል አገልግሎት በዕቅዱ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
ከፊታችን መስከረም ወር ጀምሮ የጉምሩክ ሥራዎችን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ሥርዓት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ሐምሌ ወር 21 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 110 በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ አለው።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከመደበኛ ኃላፊነቱ ጐን ለጎን ማኅበራዊና ሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱም ተጠቅሷል።